በበደል የተገፋውና በጥረቱ መሰንበት የቻለው ጫማ ሰፊ

የትምህርት ዕድል አለማግኘት፣ ምግብና መጠለያ ማጣት ከተስፋ መቁረጥ ጋር ሲደመር ድህነትን ይወልዳል። እነዚህን የሕይወት ውጣውረዶችን አልፎ በሕይወት ለመኖር የሚታትር፣ ልመናን የተጠየፈ ዜጋ ማግኘት ብዙም ያልተለመደ ነው።

የዛሬው የዚህ ዓምድ እንግዳችን እናቱ፣ እህትና ወንድሞቹ ከሞቱ በኋላ ይኖርበት የነበረውን አምስት ክፍል ቤት ጉልበተኞች ሲቀሙት ጎዳና ወጣ። ከዚያም በልመና ቢሰማራም የሰው እጅ እያዩ መኖር ስለከበደው ከስንፍና መራቅ እንዳለበትና ብርቱ ትግል ማድረግ እንዳለበት በማመን ሕይወቱን ሊያስቀጥልለት የሚያስችለውን ሥራ አንድ ብሎ መጀመር እንዳለበት አመነ።

ሁለቱም እግሮቹ ጉዳተኛ የሆኑበት የ67 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋው ይህን የሕይወት ፍልስፍናውን ወደ ተግባር መለወጥ ችሏል። ሌሎች ይማሩበት ዘንድ ያሳለፈውን የሕይወት ውጣ ውረድ እንደሚከተለው አቅርበነዋል። መልካም ንባብ።

እዝቅያስ ብሩክ ይባላል። እዝቅያስ የተወለደው እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቀበና በሚባለው አካባቢ በ1953 ዓ.ም ነበር። ለወላጆቹ የመጨረሻውና ሰባተኛው ልጅ ሲሆን አንዲት 16 ዓመት የሞላት የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሴት ልጅ አባትም ነው።

እዝቅያስ እስከ አምስት ዓመቱ እንደማንኛውም ሕፃን በእግሮቹ እየዘለለ፣ እየሮጠና እየቦረቀ ተጫውቷል። እስከ ስድስተኛ ዓመቱ ዋዜማ በእጅጉም ደስተኛ ነበር። አምስት ዓመቱን አገባድዶ ስድስተኛ ዓመቱን በሚይዝባት በዚህች ዋዜማ ዕለት እናቱ ልደቱን ሊያከብሩለት ቃል ገብተውለት ነበር።

ይሄን ታሳቢ አድርጎ ከዕድሜ አቻዎቹ ጋር ሲቦርቅ ከዋለበት ጨዋታ ወደ መኖሪያ ቤቱ የተመለሰው ቀትር ላይ እንደነበር አይዘነጋውም። ወቅቱ ጠራራ ፀሐይ ነበር። ሲመለስ ‹‹በተሰያት መውጣት ደግ አይደለም። በዚህ ሰዓት ልጅ ስብስብ ብሎ ቤቱ ነው የሚቀመጠው›› የሚለው የእናቱ ድምፅ ዛሬም በጆሮው ያቃጭላል።

ያኔ ይሄን የእናቱን ቃል ለመተግበር በዕድሜ በየደረጃው ከስድስት ዓመት ጀምሮ እስከ አንድ ዓመት የሚበልጡትን አንዲት እህቱንና አምስት ታላላቅ ወንድሞቹን ከጨዋታ ቦታው ጥሎና ቀድሞ ለመምጣት የፈለገበትም ይሄው ነበር። ከዕድሜውና ከቁመቱ በላይ ሮጧል። አሯሯጡ ቤታቸው አቅራቢያ ሲደርስ ጥልፍልፍ አድርጎ እንደጣለውም ያስታውሳል። ከዛ በኋላ የሆነውን ባያውቀውም በዚሁ ምክንያት ሁለቱም እግሮቹ ፓራላይዝ እንደሆኑ እናቱ ነግረውታል።

እናቱ እሱን ለማዳን ብዙ መከራና ስቃይ አይተዋል። ‹‹አባቴን አላውቀውም፤ አባቴ የሞተው እኔ ተረግዤ በነበረበት ወቅት መሆኑን እናቴ ነግራኛለች›› የሚለው አቶ እዝቅያስ የአባቱ በሕይወት ኖሮ እናቱን ማገዝ ያለመቻል መከራና ስቃያቸውን በእጅጉ አክብዶባቸው እንደነበርም ያወሳል። የደረሰበት የመውደቅ አደጋ ሁለት እግሩን አጥመልምሎ ፓራላይዝ በማድረግ እስከ 10 ዓመቱ በልቡ እየተሳበ እንዲሄድ አስገድዶታል።

እዝቅያስ እንዳወጋን እናቱ አምስት ዓመት ሙሉ እያዘሉት ፀበል ለፀበል ተንከራትተዋል። ሰውነታቸው በጉዳት እየኮሰመነና እየደቀቀ ሲመጣና መሸከም ሲያቅታቸው እሱን ተሸክሞ ወደ ሆስፒታልና ፀበል ለመውሰድ ጉልበት ላለው ሰው ገንዘብ ይከፍሉም ነበር። ቤት በማከራየት የሚያገኙትን ጥሪት የጨረሱትም በዚሁ ነው።

የእሱ ታላላቅ የሆኑ ልጆቻቸውን በወጉ መንከባከብ፣ ማስተማርና ማሳደግ አልቻሉም። የመጀመሪያ ልጃቸው የሞተው በዚህ ምክንያት እንደሆነም ነግረውታል። ሁለተኛው የት እንደገባ ሳያውቁ መጥፋቱንም ገልፀውለታል።

እዝቅያስ እንዳወጋን 11ኛ ዓመቱ መግቢያ ላይ መናገሻ ሱባ የምትኖረው አክስቱ ወደ ቤታቸው በመምጣት ‹እስኪ እኔ ደግሞ ላግዝሽ› በማለት ከአዲስ አበባ ወደ መናገሻ ወሰደችው። እንደ እናቱ ሁሉ ለሚሸከመው ሠራተኛ እየከፈለች ሱባ መናገሻ አካባቢ በሚገኝ ፀበል ስታስጠምቀው ቆየች። ከዓመታት በኋላም በልቡ ከመሳብ አልፎ ሁለት ክራንች ተጠቅሞ መንቀሳቀስ ቻለ።

በዚህ የተደሰተችው አክስቱ ትምህርት ቤት የመግቢያው ወቅት በደረሰበት የመውደቅ አደጋ ምክንያት በእጅጉ ቢረፍድም ትምህርት ቤት በማስገባት እስከ ስምንተኛ ክፍል አስተማረችው። ነገር ግን የስምንተኛ ክፍል ፈተና (ሚኒስትሪ) ወስዶ ወደ ዘጠነኛ ክፍል ማለፍ አልቻለም።

ፈተናውን በመውደቁ እሱም አክስቱም በእጅጉ አዘኑ። በተለይ አክስቱ አሁን ብትወድቅም በሚቀጥለው ልታልፍ ትችላለህና በድጋሚ ፈተናውን ውሰድ ብለውት ነበር። ነገር ግን በወቅቱ ፈቃደኛ አልሆነም ። ምክሯን ሊቀበላትም አልቻለም ። ድጋሚ ትምህርት አልማርም አሻፈረኝ አለ። በሁለት ክራንቹ እያዘገመ ይሰራው ወደነበረ የእረኝነት ሥራም ተሰማራ ። በዚህ ደስተኛ ያልሆነችው አክስቱ ከዓመታት በኋላ በሞት ተለየችው። በ1971 ዓ.ም እዚህ አዲስ አበባ ወዳለው ወላጅ እናቱ ቤት (ቀበና) ተመልሶ ለመምጣትም ተገደደ ።

ለሦስት ዓመታት ያህል በማብላት፣ በማጠጣት እየደገፉትና እየተንከባከቡት አብሯቸው ከተቀመጠ በኋላ ሞቱበት ። ከመሞታቸው በፊት ‹‹ልጄ ሰውና እንጨት ተሰባሪ ነው። ዘፋኙ ተማር ልጄ ያለው ዕውነቱን ነው። የተማረ ወድቆ አይወድቅምና ድንገት እኔ ብሞት እንኳን መማርህ ይጠቅምኃል፣ ትምህርትህን ቀጥል›› ብለው ቢወተውቱትም አልሰማቸውም ነበር። ‹‹ተንከራታ ያዳነችኝና እንደ እናቴ የምቆጥራት አክስቴም እናቴም ከሞቱ በኋላ በእጅጉ የተቆጨሁበት ቢኖር ይሄ ነው›› ይላል አቶ እዝቅያስ።

እናቱ ከሞቱ በኋላ እህትና ወንድሞቹ ጋር ይኖር የነበረው እዝቅያስ ሌላ ዱብዕዳ ነገር ገጠመው። ይህም “አባታችሁ ያሳደገኝ ነኝ” የምትል አንዲት የማያውቋት ሴት ቤታቸው ውስጥ ገብታ አብራቸው መኖር የጀመረች ጊዜ ነው። ይባስ ብሎ አንድ እህትና ሁለት ወንድሞቹ ተከታትለው ሞቱበት። አባታችሁ አሳደጉኝ የምትለው ሴት ብቻ በቤት ውስጥ ቀረች። ሴትየዋ በአጭር ጊዜ የቤቱ ኃላፊም ሆነች።

እናቱ በሴት አቅማቸው እናትም አባትም ሆነው የገነቡትን ቤት፣ ሰባት ልጆቻቸውን የወለዱበትንና ያሳደጉበትን አምስቱን ክፍል የግል መኖሪያ ቤታቸውንም ወርሳ በስሟ አዛወረችው። በገዛ እናቱ ቤት የተንደላቀቀ ኑሮ እየኖረች፤ እሱን ዞር ብላም አታየውም ነበር።

እዝቅያስ ምግብ የሚሰጠው እስከ ማጣት በመድረስ የሚንከባከበው ጠፋ። በእጅጉም አዘነ። ሲመረውም በ1983 ዓ.ም ወደ ጎዳና ወጣ። ለስምንት ዓመታት ያህልም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አካባቢ በሚገኘው የአውቶቡስ ፌርማታ (አውቶቡስ ማቆሚያ) ተኝቷል።

በወቅቱ በሕይወቱ ተስፋ ቆርጦ ራሱን ሊያጠፋም ቃጥቶት ነበር። የዓይጥ መርዝ ፈልጎ ሲያጣ ለመሞት ብሎ የጠጣው የተጨቀጨቀ አረፋማ ግራዋ ጭራሽ ለሆድ ሕመሙ የሚታደግ መድኃኒት ሆኖለት አረፈው። ይህ መርዝ ብሎ የጠጣው ግራዋ መድኃኒት ባይሆንለት ኖሮ እዝቅያስ ዛሬ ታሪኩን አያጫውተንም ነበር።

ራሱን ለማጥፋት ያደረገውን ሙከራ ያስተዋሉት አንዲት ሴት ድርጊቱን ዳግም እንዳይሞክር በሥላሴ ገዝተውታል። ከዚህ በኋላም እዝቅያስ ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ደጃፍ ላይ ተቀምጦ ይለምንም ነበር።

‹‹የሰው እጅ ማየት እጅግ ይከብዳል። ልመና ከስርቆት የማይሻል በጣም አፀያፊ ነው። ያሳፍራል። የሚያውቁኝ ጎረቤቶቻችን ሲያዩኝና ከንፈራቸውን እየመጠጡ ሳንቲም ሲጥሉልኝ እሳቀቅና አፍር ነበር›› ሲልም የልመናን አፀያፊ ገጽታ ይገልፀዋል።

‹‹ይሄን ያዩ ጎረቤቶቼ እኛ ምስክር እንሆንሃለን ክሰስ ቢሉኝም ትገለኛለች ብዬ ስለፈራሁና ክስ መስርቶና ፍርድ ቤት ቆሞ የመከራከር አቅም ስለሌለኝ እሺ አላልኩም›› ብሎናል። እዝቅያስ እንዳወጋን በግፍ የተቀማውን የእናቱን ቤት ጉዳይ በመርሳት ዕጣ ፈንታው የሰጠውን በፀጋ ተቀብሎ ቀሪ ሕይወቱን ለመቀጠል ጥረት ማድረጉ ላይ በረታ።

‹‹ሸክም ያለ ጤናማ እግር አይሆንም›› የሚለው እዝቅያስ ከልመና ለመላቀቅ የመጀመሪያው አማራጩና በአካባቢው የነበረው ሥራ ሸክም ቢሆንም በእግሩ በሽታ ምክንያት ሊሠራው አልቻለም። እዛው የሚተኛበት አውቶቡስ ማቆሚያ አካባቢ ሕይወቱን ለማቆየት የሚያስችለውን የሊስትሮ ሥራ በመምረጥ ጫማ መጥረግ መጀመሩንም ይናገራል።

የሊስትሮ ሥራው ከልመና እንዳወጣውና የሰውን እጅ ከማየት እንዳላቀቀው በኩራት ይገልፃል። በዚሁ አጋጣሚ ጫማ የመስፋት ሙያ ከሌሎች በሊስትሮነት ሥራ የተሰማሩ ጓደኞቹ በመቅሰም አሁን ተሰማርቶ ወደ የሚገኝበት የጫማ ስፌትና ጥገና ሥራ ገባ።

የልመና ሕይወት ተጠይፎ ጫማ በመጥረግ ኑሮውን ለመምራት የወሰነው እዝቅያስ አሁን ታዋቂ ጫማ ሰፊ ሆኗል። አሁን እዚሁ አራት ኪሎ፣ በፓርላማው መግቢያ በኩል፣ ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ደጃፍ ላይ ከአንዲት የተወጠረች ትንሽ ላስቲክ ቤት ውስጥ ተቀምጦ ጫማ እየሰፋ ሕይወቱን እየገፋ ይገኛል – ጫማ ሰፊው እዝቅያስ።

ላስቲኳ ከመወጠሯ በፊትም በቦታው ለረጅም ጊዜ ሰርቶባታል። ማደሪያውም ነበረች። ቤቷ በዝናብ ወቅት ጎርፍ ስለምታስገባ ለሥራ አትመቸውም ነበር። ዛሬም በየዕለቱ ለሚያስቸግረው ነፋስና ብርድ ተጋላጭ እንዳደረገችው ይናገራል። ሊሾ ያልተደረገበትን የአስፋልት ወለሏንም ቅዝቃዜ ችሎ በየቀኑ ግፋ ቢል ከ11 ሰዓታት በላይ በሥራ መቀመጥ እየተሳነው መጥቷል። የእግሩ ህመምም በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀሰቀስም መንስኤ ሆናበታለች።

ለዓመታት በዚህ ሁኔታ ፀሐይና ዝናብ ሲመታውና በብርቱ ሲቸገር ያዬ ሳሚ የተሰኘ አንድ ወጣት አንዲት ቆርቆሮ በቆርቆሮ ተንቀሳቃሽ ቤት ሰርቶ ሰጥቶታል። ቤቷ የተወካዮች ምክር ቤት ይዞታ በሆነው ጊቢ ውስጥ እንድትቀመጥ ተፈቅዶለት እዛ ውስጥ አኑሯታል። በዚህ ውስጥ ማደሩ ችግሩን ቀንሶለታል።

ነገር ግን ለታማሚው እግሩ ምቾት ስላልሰጠው የደሃ ደሃ ተብሎ ቤት ለማግኘት ቀበሌ ከተመዘገበ ስምንት ዓመታትን ቢያስቆጥርም ዘንድሮም አልተሰጠውም። ሆኖም ቀበሌው ኮቪድ እንዲከተብ መረጃ ከመስጠት ጀምሮ ክትባቱን ባለበት እንዲወስድ ያመቻቸለትና ሕይወቱን ከበሽታው የታደገለት በመሆኑ አብዝቶ ያመሰግናል። በተጨማሪም በየወሩ በቀጥታ ተረጂነት 350 ብር ይሰጡታል።

ይሄን ገንዘብ መኖሪያ ቤት ስለሌለው ሰው ጋር ለምኖ ላስቀመጣት ሴት ልጁ ማሳደጊያ ነው የሚያውለው። ልጅቱ የ16 ዓመት ልጅ ስትሆን ዘንድሮ ዘጠነኛ ክፍልን ደግማ እየተማረች እንደሆነም አጫውቶናል። ዘጠነኛ ክፍል የወደቀችው የሰው ቤት ኑሮ ለማጥናትም ሆነ ትምህርቷን በወጉ ለመከታተል ስላልተመቻት እንደሆነም ነግሮናል።

ዱቄትና ዘይት በቀበሌ ሲመጣ እንደማንኛውም ማኅበረሰብ ቢሰጡትም የሚያስቀምጥበትና የሚያበስልበት ቦታ ስለሌለው እንደሚሸጠው አጫውቶናል። በሽያጩ ለጫማ ሥራው የሚያገለግለው የጫማ ቀለምና የጫማ መስፊያ ጅማት ይገዛበታል። ‹‹በፊት እመገበው የነበረው ከቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን የነፍስ ይማር ሲመጣ ለምኜ ነበር፤ አሁን ላይ በጫማ ስፌት በማገኘው ገቢ የፈለኩትን ገዝቼ፣ በአቅሜ አማርጬ መብላት ችያለሁ” ሲል አጫውቶናል።

‹‹ዜጎች ትንሽ ጉልበት፣ ጥቂት ጊዜና ትልቅ ልብ ካላቸው አገር ይገነባሉ›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ በአንድ ወቅት በሚዲያ ሲናገሩ የሰማውን ደጋግሞ የሚጠቅሰው ጫማ ሰፊ በፍልስፍናው ድህነትን በመፀየፍና ከስንፍና በመራቅ ራሱን እንዳሸነፈበት ይናገራል። አሸንፎ ሕይወትን እየኖረበት ብቻም ሳይሆን እንደ ፍጥርጥሯ አድርጎ እየመራበት እንደሆነም ይመሰክራል።

በመጨረሻም እዝቅያስ እንደነገረን አቅሙን የሚመጥን የቀበሌ ቤት ቢሰጠው ወይም ቤቱን ተከራክሮ የሚያስመልስለት ቢኖር እሱ የጫማ ጠረጋና ጥገና ሙያ ሥራውን አስፋፍቶ በመተዳደር የብሩን፣ የዱቄትና ዘይቱን ድጋፍ ከእሱ ለባሰ ደሃ ለመስጠት ይፈልጋል።

ይሄን ሀሳቡን ለመተግበርም መንግሥት መኖሪያ ቤት ቅድሚያ እንዲሰጠው አልያም በማያውቃት ሴት በግፍ የተቀማውን ቤቱን ተከራክሮ በማስመለስ ረገድ እንዲተባበረው አበክሮ ይጠይቃል።

እኛም እንደ እዝቅያስ ዓይነት የሕብረተሰብ ክፍሎች የመኖሪያ ቤት ቅድሚያ እንዲያገኙና እንዲደገፉ ሳንጠቁም ማለፍ አልወደድንምና ከከተማ አስተዳደሩ ጀምሮ በተዋረድ ካለው የክፍለ ከተማ፣ የወረዳና ቀጠና ድረስ ያሉ አመራሮች ችግሩን ይሰሙት ዘንድ አቅርበነዋል።

የፍትሕ አካላትም በተለይም ከፍትሕ አካላት እንዲህ እንደ አቶ እዝቅያስ አካል ጉዳተኛና አቅመ ደካማ በሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ በደል ሲደርስ ወይም ወንጀል ሲፈፀም ክስ እስከ መመሥረት ሥልጣን ላላቸውና በየደረጃው ለሚገኙ አቃቤ ሕጎች እገዛ የሚያደርጉበትን አሠራር መዘርጋት እንደሚገባቸው ሀሳብ እያቀረብን፤ በበደል የተገፋውንና በጥረትና ትጋቱ በሕይወት መሰንበት የቻለውን አካል ጉዳተኛ – አቶ እዝቅያስ የአኗኗር ተሞክሮን ያስቃኘንበትን ጽሑፋችንን በዚሁ ደመደምን። ሳምንት በተመሳሳይ ከሌላ እንግዳ ጋር እንገናኛለን።

 ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ኅዳር   18/2014

Recommended For You