የኢኮኖሚ ጦርነቱን በድል ለመወጣት – ክረምት ከበጋ ጠንካራ ግብርና

አሸባሪው የትህነግ ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ጦርነት አውጆ ከተነሳ ድፍን አንድ አመት ተቆጥሯል። በጦርነቱም ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመቶች ተከትለዋል። ጦርነቱ በተለይም በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል በመሆኑ በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮች የግብርና ሥራቸውን በወጉ መተግበር ተስኗቸዋል። በወቅቱ እንዳይዘሩ የዘሩትንም እንዳይንከባከቡና እንዳይሰበስቡ መሰናክል ሆኗል። አብዛኞቹም ከአገር ህልውና የሚቀድም ነገር የለም በማለት ቤት ንብረታቸውንና ልጆቻቸውን ትተው ወደ ግንባር ዘምተዋል።

ይሁን እንጂ ሁሉን ትቶ ወደ ግንባር ለተጓዘው ገበሬና የገበሬ ቤተሰብ ድጋፍ በማድረግ በጉልበት፣ በገንዘብና በሀሳብ ከጎናቸው በመሆን ወገንተኝነታቸውን እያረጋገጡ ያሉ ደግሞ በርካቶች ናቸው። ከህልውና ዘመቻው ጎን ለጎንም የኢኮኖሚ ጦርነቱን በድል ለመወጣት በየአቅጣጫው የተጠናከረ የግብርና ሥራ እየተሠራ ይገኛል። የበጋ ስንዴ፣ የመስኖ እርሻ የመሳሰሉት በስፋት ወደ ትግበራ የተገባባቸው ሥራዎች ናቸው።

በሌሎች ጦርነት በሌለባቸው አካባቢዎችም እንዲሁ በጦርነቱ ምክንያት የሚደርሰውን የምርት እጥረት ለመከላከል እየተሠራ ነው። ከሰሞኑም ከኦሮሚያ ክልል በተጨማሪ በደቡብ ክልል በበጋ መስኖ የስንዴ ምርትን በከፍተኛ መጠን ለማምረትና ጦርነቱ የሚያስከትለውን ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመቋቋም እና በክረምቱ ወቅት ያልተገኘውን ምርት ለማካካስ ‹‹ቁጭት›› በሚል መርህ በክልሉ የበጋ ስንዴ መዝራት ተጀምሯል።

በአማራ ክልልም እንዲሁ በመደበኛነት ከሚታወቅበት የጤፍ ምርት በተጨማሪ በሩዝ ምርት እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ ትርጉም ያለው ሥራ መሥራት ተችሏል። በአሁኑ ወቅትም በክልሉ ሰኔ ወር ላይ ተዘርቶ የደረሰው የሩዝ ምርት ተሰብስቦ ጎተራ እንደገባም መሬቱ ለጤፍ ዘር ዝግጁ ይሆናል። ጎን ለጎንም አትክልትና ፍራፍሬ ማልማት ይቻላል።

በደቡብ ጎንደር ዞን ጤፍ፣ ጥራጥሬ እና ሌሎች የምርት ዓይነቶች የሚመረቱ ቢሆኑም የሩዝ ምርት እየተለመደና እየተስፋፋ የመጣ በመሆኑ በአካባቢው በከፍተኛ ሁኔታ እየለማ ይገኛል። ልማቱም በበጋ መስኖ ነው የሚከናወነው። የአካባቢው ገበሬ ክረምቱን በዝናብ፣ በጋውን በመስኖ የማልማቱን ሥራ ተያይዞታል። የበጋ መስኖ ልማት እየተለመደ በመጣበት በዚህ ወቅት ገበሬው ወቅትን ጠብቆ አርሶና ሰብል ሰብስቦ ጎተራ ካስገባ በኋላ ረጅሙን የበጋ ወቅት ያለሥራ ነበር የሚያሳልፈው።

የ70 አመቱ የዕድሜ ባለፀጋ በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ሊሞ ከምከም ወረዳ አንጎት ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶአደር አምሳሉ ብሩ ‹‹ምርት ሰብስበን ጎተራ ካገባን በኋላ በየድግስ ቤቱ በመዞር በመብላትና መጠጣት ነበር የምናሳልፈው። በአንድ ክረምት ብቻ የተመረተውም በቂ ባለመሆኑ በበጋው የሚያጋጥመው ችግር ከፍተኛ ነበር። ቀለብ ሲያንስ ጎመን ቀቅሎ ወደ መብላት ነበር የሚገባው። ዛሬ ግን በቂ የአመት ቀለብ ከመያዝ አልፎ ገበያ አውጥቶ በመሸጥ ገበሬው የተሻለ ቤት ሰርቶ ኑሮውን እያሻሻለ ነው› ›በማለት አጫውተውናል።

እርሳቸውም ኑሯቸው ተሻሽሎ የእርሻ በሬ ማሟላት መቻላቸውን፣ የሳር ቤታቸውን በቆርቆሮ ለውጠው ዘመናዊ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችንም ገዝተው እየተጠቀሙ መሆናቸውን ይናገራሉ። እንዲህ ያለው ለውጥና መሻሻል የታየው ገበሬው ክረምት ከበጋ በመሥራቱ እና ጊዜውን የሚያባክንበት ወቅት ወደ ሥራ በመቀየሩ ነው። የአካባቢያቸው አርሶአደር አመቱን ሙሉ በግብርና ሥራ ላይ ይገኛል። በክረምቱ ያለማውን ሰብል ሰብስቦ ጎተራ ካስገባ በኋላ በበጋው ደግሞ የመስኖ ልማቱን ይቀጥላል። በተለይ ወጣት አርሶ አደሮች በደንብ ከሠሩ ብዙ ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ነው የገለጹት።

በአካባቢው በአንድ መሬት ላይ በማፈራረቅ እየተከናወነ ያለው የተለያየ ሰብል የሩዝ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ለምርታማነትም እያገዘ መሆኑን አቶ አምሳሉ ይናገራሉ። ስለሩዝ አመራረትና እያስገኘላቸው ስላለው ጥቅምም ሲገልጹ፤ የሩዝ አመራረት ዘዴ ከሌላው የሰብል ልማት ይለያል። ሥራው ከባድ ነው። መሬቱን ሦስት ጊዜ በመገልበጥና ደጋግሞ ዘር በመዝራት ነው የሚከናወነው። ውሃና ማዳበሪያ በብዛት ይፈልጋል። ማረሱ፣ መዝራቱና የማረሙ ሥራ ድግግሞሽ ስላለው ጉልበትም ይጠይቃል።

ሥራው አድካሚ ቢሆንም ከሌሎች የሰብል ዓይነቶች ጋር ምርታማነቱ ሲነፃፀር የተሻለ በመሆኑ አርሶአደሩ መርጦት በፍላጎት ያለማል። የራሳቸውን ተመክሮ መነሻ አድርገው ስለ ውጤቱን ሲናገሩ፤ በሄክታር እስከ 40 ኩንታል የሩዝ ምርት ይሰበስባሉ። እርሳቸው ያላቸው መሬት አራት ጥማድ በመሆኑ እንጂ ሰፊ የእርሻ መሬት ያለው ገበሬ ብዙ አምርቶ ተጠቃሚ ይሆናል። የአንድ ኪሎ ሩዝ ዋጋ ከአንድ ኪሎ ጤፍ አይበልጥም። ነገር ግን የምርት ብዛቱ ከፍተኛ በመሆኑ ነው ሩዝ ተመራጭ የሆነው። ጤፍ የሩዝ ምርትን ያክል አይሆንም። የሩዝ ምርት በገቢ ደረጃ ጥቅሙ ከፍተኛ ሆኖ ነገር ግን በአመት አንዴ ብቻ ነው የሚመረተው። ምክንያቱ ደግሞ ሩዝ ሲመረት የውሃ ፍጆታው ከፍተኛ ነው። በአካባቢው የሚገኘው ውሃ ደግሞ በቂ አይደለም።

አቶ አምሳሉ እንዳሉት፤ የሩዝ ልማት ፎገራ በሚባለው አካባቢ ነበር በስፋት የሚታወቀው። ቀስ በቀስ ነው ወደ እርሳቸው የመኖሪያ አካባቢ የተስፋፋው። የሩዝ ምርታማነት ከፍተኛ ሆኖ አርሶ አደሩም በፍላጎት እያለማው ነገር ግን የልማቱ ሥራ በቴክኖሎጂ አልታገዘም። ዛሬም ድረስ በሬ ጠምደው ነው የሚያርሱት።

ስሜታቸውን እንደተረዳሁት በቴክኖሎጂ (በክላስተር) የታገዘ ልማት ባለመሆኑ ቅር አሰኝቷቸዋል። የሩዝ ልማት ሥራ ከፍተኛ ድካም የሚጠይቅ በመሆኑ በቴክኖሎጂ ቢታገዝ ድካማቸውን ይቀንስላቸዋል። ከሰብል፣ ከሩዝ፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ጎን ለጎን በአካባቢው የባህርዛፍ ተክል ልማት በስፋት ይከናወናል። ለማገዶና ለቤት ሥራ አስፈላጊ በመሆኑ ባህርዛፍ ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል። በተለይ ማገዶ በቅርበት ካልተገኘ ተሰብስቦ የገባው ምርት በሙሉ ለማገዶ ግዥ ውሎ ድካማቸው ከንቱ እንዳይቀር ነው ከወዲሁ ትኩረት የሰጡት። ገበያ ላይ ውሎም ተጨማሪ ገቢ ያስገኛል። የአንድ አጣና ዋጋም ከ150 ብር በላይ በመሆኑ ጥቅሙ ከፍ ያለ ነው ።

በመስኖ ልማቱ ስለሚያጋጥማቸው ችግርና የገበያ ትስስር አቶ አምሳሉ እንደገለጹት፤ መስኖ ለመጠቀም ውሃ ከወንዝ በስበት ኃይል ለማውጣት ነዳጅ ያስፈልጋል። ነዳጁ በተፈለገ ጊዜ በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት አይቻልም። ማዳበሪያም ከአትራፊ ነጋዴ ላይ እየገዙ መጠቀማቸውም ችግሩን ተደራራቢ አድርጎታል። እርሳቸው እንዳሉት አንድ ቁምጣ ማዳበሪያ ከነጋዴ እስከ 1500 ብር ገዝተው ይጠቀማሉ። የህብረት ሥራ ማህበር ዩኒየን በ800 ብር የሚያቀርብ ቢሆንም አቅርቦቱ የተቆራረጠ ነው። የገበያ ትስስሩም እንዲሁ ክፍተት አለበት። በአካባቢያቸው የህብረት ሥራ ዩኒየን ቢኖርም የሚሰጣቸው ዋጋ የድካማቸውን ያህል ባለመሆኑ ከሸማቹ ጋር ቀጥታ መገበያየቱን ይመርጣሉ።

ኢትዮጵያ የህልውና ዘመቻ ላይ በምትገኝበት በዚህ ወቅት ደቡብ ጎንደር ላይ የጎላ የፀጥታ ችግር ባይኖርም ከግብርና ሥራው ጎን ለጎን አካባቢ ነቅቶ በመጠበቅ ነዋሪዎች በተጠንቀቅ ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ። በተለይም ከአካባቢያቸው ወደ ደብረታቦርና የተለያዩ አካባቢዎች የሚያሸጋግረው የርብ ድልድይ በአሸባሪው ሕወሓት ቡድን እንዳይጎዳ እንዲሁም የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ተጠቅመው ለዘረፋ የሚመጡትን ለመከላከል እየጠበቁ መሆናቸውን ይናገራሉ። ከአካባቢያቸው የዘመቱ ገበሬዎችን እርሻም ተባብረው በማረስ፣ ሰብል በመሰብሰብ ላይ እንደሚገኙ አቶ አምሳሉ ይገልጻሉ።

ከግብአት አቅርቦትና ከገበያ ትስስር ጋር በተያያዘ ያነሷቸውን ቅሬታዎችና በአጠቃላይ የዞኑን የሩዝ ልማት በተመለከተ ደግሞ የደቡብ ጎንደር ዞን የሊሞ ከምከም ወረዳ አንጎት ቀበሌ ግብርና ጽሕፈት ቤት የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ጌታቸው ሹመት እንደሚከተለው አስረድተዋል።

እርሳቸው እንዳሉት በሊሞ ከምከም ወረዳ የተለያየ ዝርያ ያላቸው የሩዝ ልማት በስፋት በመከናወን ላይ ይገኛል። ዝርያዎቹም‹‹ኃይላንድ ራይዝ›› እና ‹‹ሎውላንድ ራይዝ›› በመባል ያታወቃሉ። ‹‹ኃይላንድ ራይዝ›› የሚባለው ዝርያ ውሃ በመጠኑ የሚፈልግ ሲሆን፣ ‹‹ሎው ላንድ ራይዝ›› ደግሞ ከፍተኛ የውሃ መጠን የሚያስፈልገው ነው። በዚህ መልኩ ተስማሚ በሆነ ቦታ እንዲለማ ይደረጋል። ምርታማነታቸውም እንዲሁ የተለያየ ነው። ‹‹ሎው ላንድ ራይዝ›› በሄክታር እስከ 70 ኩንታል ሲሆን፣ ‹‹ኃይላንድ ራይዝ›› ደግሞ በሄክታር እስከ 50 ኩንታል ምርት ይሰበሰባል።

በአጠቃላይ በሊሞ ከምከሞ ወረዳ ቡራ ተብሎ በሚጠራ ቀበሌ እስከ 900 ሄክታር፣ አንጎት ቀበሌ 750 ሄክታር፣ ሽና ደግሞ እስከ 1400 ሄክታር መሬት ላይ ሩዝ በስፋት ይለማል። እነዚህ ከፍተኛ አምራች ተብለው ይለዩ እንጂ በሌሎችም የወረዳው አካባቢዎች በመልማት ላይ ይገኛል።

የሩዝ ዝርያዎቹ ለአርሶ አደሩ የሚከፋፈለው በደቡብ ጎንደር ውስጥ ከሚገኝ ጉና ከሚባለው ዘር አምራች ድርጅት፣ የዘር ብዜት ከሚያከናውኑ አርሶ አደሮችና ከሌሎችም ዘር አምራቾች ሲሆን፣ ዘሩን በጥራት ከሚያመርቱ አምራቾች ለማከፋፈል ጥረት ይደረጋል። የሩዝ ልማት ውሃ የሚፈልግ በመሆኑ በቅድሚያ የእርሻ መሬቱ ውሃ የሚገኝበት አካባቢ መሆኑ ይረጋገጣል። በባለሙያ የተሰጠ ምክርን መሠረት ባደረገ ተገቢ የሆነ ማዳበሪያና ተመሳሳይ የሆነ የምርጥ ዘር መጠቀም፣ በመስመር መዝራት፣ በድግግሞሽ ማረስ፣የበሽታ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ መከናወን ካለባቸው ተግባራት መካከል ይጠቀሳሉ። ውሃ በአግባቡ ለመጠቀምና ለባለሙያ ክትትል፣ ድጋፍና ቁጥጥር እንዲያመች እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ ይመረጣል። ልማቱ በዚህ መንገድ እንዲካሄድም ጥረት እየተደረገ ነው።

ሩዝ ለማልማት አርሶአደሩ ስላለው ፍላጎትም አቶ ጌታቸው እንዳስረዱት፤ ሩዝ ከሌሎች የሰብል ዓይነቶች የሚለየው በፀረተባይ የመጠቃት ዕድሉ ጠባብ ነው። ከአነስተኛ ማሳ ከፍተኛ ምርትም ይገኛል። እነዚህ አርሶአደሩ ሩዝ የማምረት ፍላጎት እንዲኖረው ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳል። በአሁኑ ጊዜም ፍላጎቱ ከዕለት ወደዕለት እየጨመረ ነው።

በሩዝ ልማቱ ላይ አቶ ጌታቸው በተግዳሮትና  በጥንካሬ ያነሱት በ2013/2014 የምርት ዘመን የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት፣ የሩዝ ምርት ከውሃ ጋር የተያያዘ በመሆኑ በምርት ዘመኑ በቂ ውሃ ባለመኖሩ በሚፈለገው ያህል አለመመረቱ፣ የተለያየ ዝርያም እንዲሁ ፍላጎትን ያሟላ አለመሆኑ ጥቂቶቹ ናቸው። በጥንካሬ ደግሞ ከዚህ ቀደም ለሩዝ ልማት ያልዋለ መሬት ውሃ በማቆር ሩዝ ለማልማት ጥረት መደረጉ በአርአያነትና በመልካም ጎን ይጠቀሳል። የአርሶአደሩን ገቢ በማሻሻል እያስገኘ ያለው ጥቅም መዘንጋት የለበትም። የአካባቢው መሬት ለሩዝ ልማት ተስማሚ መሆኑ፣ ተረፈ ምርቱም ለከብት መኖ እና በከሰል መልክ ለማብሰያ ስለሚውል ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነው።

ስለገበያ ትስስርና በግብአት አቅርቦት ላይም ስለተነሳው ቅሬታም አቶ ጌታቸው ምርቱ ከሚመረትበት ቦታ እስከ ተጠቃሚው ድረስ የገበያ ትስስር ተፈጥሯል ብለው አያምኑም። አርሶአደሩ ከህብረት ሥራ ዩኒየኖች ጋር ያለው ትስስርም ጠንካራ እንዳልሆነ ይገልፃሉ። ዩኒየኖቹም ከሁሉም አርሶአደሮች ምርቱን የመግዛት አቅማቸው ሊፈተሽ ይገባል ይላሉ። እርሳቸው እንዳሉት ብዙ ሥራ መሠራት አለበት። አምራቹንና ነጋዴውን የማገናኘት፣ ሌሎች አገሮች እንደሚያደርጉት ምርቱ የተመረተበትን አካባቢና ስለምርቱ መግለጫዎችን በማድረግ እሴት የተጨመረበት ምርት ማቅረብ ይጠበቃል። አሁን ባለው ምርቱ ለገበያ ይቀርባል እንጂ የማን እንደሆነ አይታወቅም።

ከግብአት አቅርቦት ጋር በተያያዘ እንደገለጹት፤ በ2013/2014 የምርት ዘመን ካልሆነ በስተቀር የማዳበሪያም ሆነ የምርጥ ዘር አቅርቦት እንደክፍተት የሚነሳ ጉዳይ አይደለም። በህብረትሥራ ማህበራት አማካኝነት በተገቢው እየቀረበ ይገኛል። አንድ ኩንታል ማዳበሪያ በ1600 ብር ነው የሚቀርበው።

በንጽጽር ሲታይ አርሶደሮች ተጠቃሚ ናቸው። በውሃ አጠቃቀምም ቢሆን፣ የሩዝ ሰብል ውሃ የሚያስፈልገው ሰብሉ ሲደርስ በመሆኑ ውሃ በጀነሬተር ኃይል መሳብ የሚያስፈልገው በዚህ ወቅት ነው። በመሆኑም ከፍተኛ የሆነ ነዳጅ አያስፈልግም። የውሃ መሳቢያ ሞተር አቅርቦት ችግር ግን አለ። የህብረት ሥራ ማህበራት እያቀረቡ አይደለም። ይሄ ለወደፊት መታየት ይኖርበታል። የምርጥ ዘር አቅርቦትም ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ ነው። በቅርብ ጊዜ ያጋጠመው የማዳበሪያ አቅርቦትም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ካጋጠመው ጦርነት ጋር በተያያዘ እንደአገር ትኩረቱ ወደዚያ በመሆኑ ነው።

የተጨማሪ ሰብል ልማትና ያልተቋረጠው የአርሶአደሩ ክረምት ከበጋ የግብርና ሥራ ለምርትና ምርታማነት ማደግ እንደአገር በምግብ እህል እራስን ለመቻል እየተደረገ ላለው ጥረት ስኬት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማዳከም ተኝተው ለማያድሩ ወገኖችም ምላሽ እየሰጠ ይገኛል።

ኢትዮጵያ የህልውና ዘመቻ ላይ በምትገኝበት በዚህ ወቅት ለአሸባሪው ሕወሓት ቡድን ወግነው የተለያየ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላት በተለይም አሜሪካን ግልጽ የሆነ የኢኮኖሚ ጫናዋ ዓለም ያወቀው ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ የተጋረጠባትን ፈተና መወጣት የምትችለው ደግሞ የጀመረችውን የግብርና ሥራ አጠናክራ በመቀጠል ነው።

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ኅዳር 20/2021

Recommended For You