ትምህርት ቤቶችን ለፖለቲካ ሴራ

ትምህርት ቤት የእውቀት መቋደሻ ማዕድ ነው። ተማሪዎች ፊደል ቆጥረው፣ ቁጥር ቀምረው፣ ተመራምረው እና ታሪክን ጠቅሰው ሙሉዕ ስብዕና ለማግኘት የሚቀረጹበት አውድ፤ የመማር ማስተማር ተግባር የሚከናወንበት ወይም የእውቀት ሽግግር የሚደረግበት ቦታ ነው።

ተማሪዎች በሚያገኙት አዳዲስ እውቀት የአስተሳሰብ አድማሳቸውን የሚያሰፉበት፤ የአሠራርና የባህሪ ለውጦችን የሚያደርጉበት፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ አካባቢያቸውንና ዓለምን በቅጡ የሚረዱበት የእውቀት ገበታ፤ የእውቀት ምንጭ ነው ትምህርት ቤት። እውቀት ሳይንሳዊ ወይም ምክንያታዊ በሆነ ማረጋገጫ የሚቀርብበት፤ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ቆይታቸው ከትናንት ይልቅ ዛሬ፣ ከዛሬ ይልቅ ነገ፣ ከነገ ይልቅ ከነገወዲያ በእውቀት እየጎለበቱና አእምሯዊ እድገት እያሳዩ የሚሄዱበት ሥፍራ ነው።

ታዲያ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ የኢትዮጵያን ሰላም እያወኩ ያሉ የውጭ እና የውስጥ ኃይሎች ትኩረታቸውን ትምህርት ቤት ላይ አድርገው የእኩይ ተግባራቸው ማስፈጸሚያ ሲያደርጓቸው ተስተውሏል።

አሸባሪዎቹ የሕወሓት ታጣቂ ኃይሎች በወረሯቸው የአማራና አፋር አካባቢዎች ጉዳት ካደረሱባቸው አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ ትምህርት ቤት አንዱ ነው። አሸባሪው ቡድን በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በትምህርት ቤቶች ላይ ብቻ ያደረሰው ውድመት ለማመን የሚከብድ እንደነበር ቀደም ሲል ከቀረቡ ሪፖርቶች መስማታችን ይታወሳል። ይህ አጥፊ ቡድን ዛሬ የተስፋፋባቸውን አዳዲስ ዞኖችና አካባቢዎች ስናስብ ደግሞ በትምህርት ቤቶች ላይ ምን ያህል ውድመት ሊያደርስ እንደሚችል መገመት አይከብድም።

አሸባሪው የሕወሓት ቡድን መማሪያ ክፍሎችን በከባድ መሣሪያ በማውደም፤ ጣሪያቸውን በመገንጠል፤ ወንበሮችን እየሰባበረ ለማገዶነት በመጠቀም፤ የተማሪዎችን ፋይል ከጥቅም ውጪ በማድረግ፤ የመማሪያ መጻሕፍትን በመቀዳደድ፤ ከፍተኛ ወጪ የወጣባቸውን ፕላዝማዎች በመሰባበርና በመዝረፍ፤ ቅጥር ግቢውን የጦር ካምፕ እና ማሰልጠኛ በማድረግ ትምህርት ቤቶች ማንሰራራት እንዳይችሉ አድርጎ አውድሟቸዋል። በርካታ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች አካባቢያቸውን ትተው እንዲሰደዱ፤ መምህራንም ያለሥራ እንዲቀመጡና ለችግር እንዲዳረጉ አድርጓል።

 አሸባሪ ቡድኑ ሆነ ብሎ ትምህርት ቤቶችን እንዳልነበሩ በማድረግ ለአሁን ብቻ ሳይሆን ለመጪውም እንዳይንሰራሩ አድርጓል።

በጦርነት ቀጣና የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ላይ እንዲህ ዓይነት ውድመት በመፈጸም የመማር ማስተማር ሂደት እንዳይኖር ሲያደርግ ተባባሪዎቹ የውጭ ኃይሎችም ጦርነት በሌለባቸው ሰላማዊ አካባቢዎች የመማር ማስተማሩን ሂደት ለማደነቃቀፍ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ሲያሰራጩ ታዝበናል።

ይህንን ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች አዲስ አበባ የጸጥታ ስጋት አለባት የሚለውን የውጭ ሚዲያዎች የሀሰት ፕሮፓጋንዳ መነሻ በማድረግ ትምህርት ለማቆም ተዘጋጅተው እንደነበር የሚታወቅ ነው።

በተለይም ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤቶች የሚሰጣቸውን ቀጥተኛ ተልእኮ ለመፈጸም ከመንግሥት እውቅና ውጪ ትምህርት እስከማቋረጥ ደርሰዋል።

ምዕራባውያን በከተሞች ያለውን የመማር ማስተማር ሂደት ለማደነቃቀፍ የሞከሩት የኢትዮጵያ መንግሥት ነገሮች ከቁጥጥሩ ውጪ እንደሆኑ፤ የአሸባሪው ቡድን ተጽእኖ እንደበረታ፤ ከተሞችም የጸጥታ ስጋት እንዳለባቸው ለማስመሰል ነው። በዚህምየውጭ አገር ዜጎች አገሪቱን እየለቀቁ እንዲወጡ፤ መንግሥትና ሕዝብ ተስፋ እንዲቆርጡ በማድረግ አሸባሪው ቡድን ሥልጣን እንዲጨብጥ ያለመ ሴራ ሲፈጽሙ ከርመዋል።

እንግዲህ ለሰው ልጆች ፍትህ፣ ዲሞክራሲና ነፃነት ቆመናል፤ ከአፍሪካ ጋር በትብብር እንሠራለን፤ ትምህርት እንዲስፋፋ ድጋፍ እናደርጋለን የሚሉት ምዕራባውያን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ጉዳይ ከቁም ነገር ሳይቆጥሩ በዚህ ልክ ትምህርት ቤቶች ላይ ሲያሴሩ ማየታችን የሚያስገርም ነው።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሣ ባለፈው ሳምንት ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክተው በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ እንዳሳወቁት፣ ሕወሓትና ተባባሪዎቹ ትምህርት ቤቶች ላይ ትኩረት አድርገው መሥራታቸውን ተናግረዋል። እንደመሣሪያ የሚጠቀሙት የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት መሆኑን ገልጸዋል።

የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት አገር የማፍረስ ዓላማቸውን ለማሳካት ይጠቅመናል ብለው ያለምንም ሀፍረት በትኩረት እየሠሩበት ያለ አንድ የጦር መሣሪያ መሆኑን ጠቅሰዋል። የሰዎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ ለማወክ ዓለምአቀፍ ሚዲያዎችን እየተጠቀሙ በጣም በርካታ ሥራዎችን ሲሠሩ እንደነበርም አስታውሰዋል።

የሽብርተኛው ወራሪ ኃይልና አለንልህ የሚሉት ምዕራባውያን ትኩረት ካደረጉባቸው ዘርፎች አንዱ ትምህርት እንደሆነ ተናግረዋል። አሸባሪው ቡድን ከዚህ በፊት በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በትምህርት ተቋማት ላይ የፈጸመው ውድመት የሚታወስ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ ምዕራባውያን በተለይም አዲስ አበባ ላይ የሚገኙ የማኅበረሰብና ዓለምአቀፍ ትምህርት ቤቶች በሀሰተኛ መረጃዎች ጫና እንዲያድርባቸው እና የመማር ማስተማር ሥራቸውን እንዲያቆሙ ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በዚህ የተነሳም ጥቂት የሚባሉ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራቸውን ለተወሰነ ጊዜ እንዲያቆሙ አድርጓቸዋል ብለዋል። የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ባደረገው ክትትልና ወላጆችም ባቀረቡት ቅሬታ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ሥራቸውን አቁመው እንደነበር ታውቋል።

ትምህርት ሚኒስቴር የተነዛውን ሀሰተኛ መረጃ ተንተርሰው የመማር ማስተማር ሥራቸውን እንዳያቋርጡ ለሰባት የማህበረሰብ ትምህርት ቤቶች እና ለአስራ ዘጠኝ ዓለምአቀፍ ትምህርት ቤቶች በደብዳቤ ማሳወቁን ተናግረዋል። ከነዚህ ውስጥ

 የተላለፈውን መመሪያ ችላ ብለው ሥራቸውን በይፋ ያቋረጡ ሦስት ዓለምአቀፍ እና የማኅበረሰብ ትምህርት ቤቶች የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ በይፋ እንዲደርሳቸው መደረጉን ጠቅሰዋል። ትምህርት ቤቶቹ በውጭ አገር ዜጎች የሚተዳደሩ እንደመሆናቸው መደበኛውን የመማር ማስተማር ሂደት በማስተጓጎል አዲስ አበባ የጸጥታ ችግር አለባት የሚል መልዕክት ማስተላለፍ እንዲችሉ ታስቦ የተወጠነ ሴራ ነበር። እነዚህ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ትምህርት ቤቶችም አንደኛ የሳንፎርድ ዓለምአቀፍ ትምህርት ቤት፣ ሁለተኛው የቤንግሃም ትምህርት ቤት እና ሦስተኛው የዓለምአቀፍ ኮሚኒቲ ትምህርት ቤት በተለምዶ (የአሜሪካ ትምህርት ቤት) የሚባለው መሆናቸውን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ትምህርት ቤቶቹ አሁን ላይ የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ የኦን ላይን እና የገጽ ለገጽ ትምህርት መስጠት መጀመራቸውን ትምህርት ሚኒስቴር ባደረገው ዳሰሳ ማረጋገጡን ገልጸዋል። በኅብረተሰቡ ላይ መደናገር ለመፍጠር እየተደረጉ ካሉ ጥረቶች መገንዘብ የሚቻለው የተቀናጀ ሀሰተኛ መረጃን በማስተላለፍ የማዕከላዊ መንግሥቱን አቅም በማሳነስና የሕዝቡን ሥነ ልቦና በማዳከም አገርን የማሸበር ዓላማ ያለው ነው። ጦርነቱ ግንባር ላይ ብቻ እንዳልሆነና የውጭ ኃይሉም በማዕከላዊ መንግሥት ላይ ጫና በመፍጠር ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር እየተናበቡ የሚሠሩ መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ሕዝቡ እያንዳንዱን ሴራ እየተረዳ በመምጣት አንድነቱን አጠናክሮ አገሩን ከጠላት ለመታደግ እያደረገ ስላለው ርብርብም መንግሥት እንደሚያመሰግን ገልጸዋል። አሸባሪ ቡድኑና ተባባሪዎቹ የውጭ ኃይሎች ከግንባር እስከ መዲናዋ ድረስ በትምህርቱ ዘርፍ ላይ እያሳደሩ ያለው ጉዳትና ዘርፉን የፖለቲካ ፍላጎታቸው ማስፈጸሚያ ለማድረግ ምን ያህል ሊጠቀሙበት እንደሞከሩ የሚያሳይ ነው።

ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በእውቀትና በመልካም ስብዕና የሚቀረጹባቸው እንጂ የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚዎች እንዳልሆኑ ኅብረተሰባችን ይገነዘባል። ወትሮም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተነሱ ኃይሎች የትምህርት ሥርዓቱን ማስተጓጎል አንዱ እቅዳቸው መሆኑን በተግባር ስላሳዩን በወጥመዳቸው ላለመያዝ መንቃት ይኖርብናል። መምህራን ተማሪዎችና ሌሎቻችንም የኅብረተሰብ ክፍሎች በትምህርቱ ዘርፍ ያነጣጠረውን አገር የማፈራረስ ሴራ ለማምከን ሁልጊዜ የጠላቶችንን እንቅስቃሴና ተግባር እያስተዋልን አስፈላጊውን ምላሽ መስጠት ይኖርብናል።

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ኅዳር 20/2021

Recommended For You