ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር የተሰለፋችሁ እጃችሁን በመስጠት ውድ ሕይወታችሁን አትርፉ !

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ሳይወዱ በግድ የገቡበትን የህልውና ዘመቻ በድል ለማጠናቀቅ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሰዋል። በተለይም የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የህልውና ዘመቻውን በጦርነቱ ግንባር ከተቀላቀሉና ጦሩን በአካል ተገኝተው መምራት ከጀመሩ ጀምሮ እጅግ አስደናቂና አስደማሚ ድሎችን በአጭር ቀናት ማየት ተችሏል።

አሁን የጠላት ጦር የሚገባበት ጉድጓድ ጠፍቶታል። በደመ ነፍስ የቻለውን ዘርፎ፤ ያልቻለውንም አውድሞ ለመሸሽ እየሞከረም ይገኛል። በስሜትና በእውር ድንብር ፈርጥጦ እንደገባው ፈርጥጦ መውጣት ግን አልቻለም። መውጪያ ቀዳዳ ሲያጣም የማርያም መንገድ አሰጡን ሲልም ጀሌዎቹን በምልጃ መማጸኑን ተያይዟል። ይሁንና ይሄ ፍጹም የማይሆን የቁም ቅዠት ነው።

የእናት ጡት ነካሽ የሆነው አሸባሪው ሕወሓት ታሪክ ይቅር በማይለው አሳፋሪ ሥራው ፣ ባሰቃያቸውና በደፈራቸው ሴቶች፣ ህይወታቸውን ባሳጣቸው ንጹሐንና ባወደመው ሀብት ንብረት ልክ መቀጣት አለበት። ለዚህም ሲባል እጁን በሰላም መስጠት፤ ይህን ካላደረገም ዕርምጃ ሊወሰድበት ግድ የሚልበት ጊዜ ላይ ተደርሷል።

አሁን ጦርነቱ በመገባደድ ላይ ነው፤ የጠላት ጦርም በወገን ጦር ተከቦ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ሰዓት ላይ ነው። በመሆኑም መንግሥት በተደጋጋሚ እንደሚያደርገው ሁሉ በጦርነት ግንባር የተሰላፋችሁ ሁሉ መሳሪያ አውርዳችሁ እጃችሁን በሰላም ስጡ፤ ህይወታችሁን አትርፉ ሲል የመጨረሻ ዕድል ሰጥቷል።

ሳይወዱ በግድ በኮታ ከየቤታቸው ልጆቻቸውን ለጦርነቱ እንዲገብሩ የተደረጉ የትግራይ እናቶችም ልጆቻችን የታሉ ሲሉ እንዲጠይቁና ልጆቻቸውን ከዓላማ ቢስ ሞት እንዲታደጉ ጥሪ አቅርቧል።

የትግራይ እናቶች ሳይወዱ በግድ የርዳታ ምግብ እንድታገኙ፣ ከየቤቱ በኮታ አንድ ሰው አምጡ እየተባሉ በማስፈራሪያ ልጆቻቸውን ላልተፈለገ ጦርነት ዳርገዋል። ዕድሜያቸው ለውትድርና ያልደረሱ ልጆቻቸውን ላላመኑበት ጦርነት ገብረዋል ፤ አሁንም እየገበሩ ናቸው። በስንት መከራና ስቃይ ተምረው ዲግሪ የያዙ መሥራትና መለወጥ የሚፈልጉ፣ ሳይማር ያስተማራቸውን ቤተሰብ ለመጦር የተመኙ ፣ ነግደው ማትረፍንና ማደግን የሚያስቡ ታዳጊዎችና ወጣቶች ሁሉ በቂ የወታደራዊ ስልጠና ሳያገኙ ለጦርነቱ እንዲሰለፉ ተደርገዋል።

አቅማቸውም፣ ብቃታቸውም ጦርነቱን መቋቋም ባለመቻላቸው ብዙዎች በገፍ አልቀዋል። ነገ ጦርነቱ በድል ሲጠናቀቅ እናቶች ልጆቻቸውን ባለቤቶቻቸውን በማጣት ፊታቸው በዕንባ መታጠቡና አንጀታቸው በቁጭት መክሰሉ የማይቀር ነው። ኀዘኑ የበለጠ የከፋ እንዳይሆን ግን ዛሬ በጠላት ጦር ግንባር ተሰልፈው ያሉትን ለማትረፍ እንዲቻል መንግሥት ያቀረበውን የእጅ ስጡ ጥሪ ሊቀበሉ ይገባል። እናቶች ለማንፈልገው ሀገርን የማፍረስ ዓላማ ልጆቻችን አይለቁ ብላችሁ ድምፃችሁን አሰሙ። በቃን ብላችሁ አደባባይ ውጡ፣ በህልውናችሁ የመጣውን ሀገር አፍራሽ ጠይቁ ተቃወሙ።

የሃገር ጠላት ከሆነው አሸባሪው ሕወሓት ጋር በየግንባሩ የተሰላፋችሁ ወጣቶችም የነገውን ህይወታችሁን አስባችሁ ድሉም በአጭር ጊዜ በኢትዮጵያውያን እንደሚጠናቀቅ ተገንዝባችሁ ታሪክ የሌለው ሞት አትሙቱ ፤በቃን ብላችሁ ትጥቅ ፍቱ፤ በሰላምም እጃችሁን ለመንግሥት ስጡ።

የአሸባሪው ሕወሓት ቡድንም ሆነ እሱን የሚጋልቡት አንዳንድ የውጭ ኃይሎች ዋና ዓላማቸው ሀገርን ማፍረስ ነው። በኢትዮጵያ ምድር ተላላኪ መንግሥት መመስረትና እንደልባቸው መዝረፍ ነው። በሀገራችን ጠንካራ የመንግሥት ስርዓት እንዳይኖር ሲጠሩት አቤት ሲልኩት ወዴት የሚል ተላላኪ ማስቀመጥም ሌላው ዓላማቸው ነው። ይሄንን የሀገርን ሉዓላዊነት የሚዳፈርን ዕሳቤ ደግሞ ማንም ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ አይቀበለውም።

አሸባሪው ሕወሓት የቆሰቆሰው ጦርነት አንዳችም የሚፈይደው ነገር የለም። መነሻውም መድረሻውም ሀገር ማፍረስ ነው። ሀገር ማፍረስ ደግሞ ሰይጣናዊ አስተሳሰብ ነው። ሀገር ሲፈርስ እኔ እጠቀማለሁ ከሚል ጥቂት ቡድኖች የሚነሳ ሃሳብ ነው። ጤነኛ አዕምሮ ኖሮት ይሄንን ሃሳብ ለማሳካት የሚተባበር የለም፤ አይኖርምም። ይልቁንም ሀገር አፍራሹን ቡድን ለመደምሰስ በሚደረገው የህልውና ዘመቻ ሁሉም እንደአቅሙ ተባብሯል እንጂ።

ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ድረስ ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ ፤እውቀት ያለው በእውቀቱ ሀገሩን ለመታግ በመደገፍ ላይ ነው። በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ደጋፊዎች ሁሉ በአንድ ድምፅ ከኢትዮጵያ ላይ እጃችሁን አንሱ ሲሉ ድምፃቸውን እያሰሙ ናቸው።

አሁን ጦርነቱ በኢትዮጵያውያን ብርቱ ክንድ ወደ መጠናቀቁ ደርሷል። የጠላት ጦር እያጣጠረ ይገኛል። ከጣሩ ለመውጣት በቀረችው አጭር ጊዜ እጃችሁን በመስጠት ውድ ህይወታችሁን አትርፉ። የትግራይ እናቶችም ልጆቻችን የታሉ ብላችሁ ጠይቁ፤ ከእልቂት የተረፉት ታዳጊዎችና ወጣቶች ለዘር አትርፉ ፤ ለሃገር አፍራሾች ከንቱ ሴራ ልጆቻችንን አንገብርም በቃንም በሉ!

አዲስ ዘመን  ኅዳር  22/2014

Recommended For You