መላ ኢትዮጵያውያን በምንከፍለው ውድ ዋጋ አገራችን ጸንታ ትቆማለች!

የኢትዮጵያውያን መታወቂያችን ጀግንነት ነው። ጀግንነት ከጥንት አያት ቅድመ አያቶቻችን የወረስነው፤ ከደም ከአጥንታችን የተዋሃደ መለያችን ነው። ይሄንን የጀግንነት ታሪካችንን ታሪክ ሠሪዎቹ አባቶቻችን ደግመው ደጋግመው ነግረውና፤ በተግባር አሳይተውናል።

አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍስሰው ለእናት አገር መሞት ሞት ሳይሆን ጀግንነት መሆኑን በተግባር አሳይተውናል፤ በውስጣችንም አስርጸዋል።

እናም እናት አገር ተደፈረችና ወራሪ ጠላት ተነሳባት ሲባል ሆ ብለን ቀፎው እንደተነካበት ንብ በጋራ እንተማለን። ወንድ ሴት፣ ልጅ አዋቂ፣ መሪ ተመሪ ሳንል፤ የቋንቋ የሃይማኖት ልዩነት ሳናደርግ በመሰዋዕትነታችን የአገራችንን ዳር ድንበር ለማስከበር እንዘምታለን። ቆላ ደጋ፤ ወንዝና ሸንተረር ሳንል አንድነታችንን አጠንክረን የአገራችንን ሉዓላዊነት የተዳፈረውን፣ ቀኝ ሊገዛ የመጣውን፤ አገር አፈርሳለሁ መሬት እቆርሳለሁ ብሎ የተነሳውን የውጭ ጠላትና የውስጥ ባንዳ በአንድነት አንበርክከን አይቀጡ ቅጣት ቀጥተን ጭምር ታሪካችንን በወርቅ መዝገብ አስፍረናል።

በአገራቸው የነጻነት ታሪክ ላይ ማህተማችንን አትመናል። ይሄ እውነተኛው ታሪካችን ከዘመን ዘመን ተሻግሮ ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያውያን የጀግንነት ስሜት፣ ወኔ እና ድል አድራጊነት አብሮን ቀጥሏል። ዛሬም ይሄንኑ ጀግንነት እየደገምነው እንገኛለን። ከውጭም ሆነ ከውስጥ የመጣብንን ጠላት ለመመከት ሆ ብለን ተነስተናል፤ የአገርን የጥሪ ድምጽ ተቀብለን ሆ ብለን ከተናል።

ጠላትን አይቀጡ ቅጣት እየቀጣን አንጸባራቂ ድል የምንጎናጸፍበት ጊዜው ተቃርቧል። በጀግንነት በመቆምና መሰዋዕትነት በመክፈል አገራችንን እንደ አለት እናጸናለን። ለማንም የውጭ ጠላት የማትንበረከክ በቀላሉ የማትጠመዘዝ አገር መሆኗን ጥንት ብቻም ሳይሆን አሁንም ደግመን ደጋግመን እናስመሰክራለን። ኢትዮጵያን ለማንበርከክ፣ የመሪዎቿን እጅ ለመጠምዘዝና ሕዝቧን ለማሸበር እንደነአሜሪካ እና አንዳንድ ምዕራባውያን ያሉ አገራት ከነመገናኛ ብዙኃኖቻቸው ቢነሱብንም ኢትዮጵያውያን ግን ሞት አንዴ ነው፣ ሞት ለነፃነት ሲሆን ሞት አይደለም፣ አገሬ ከምትደፈር ሞቴን እመርጣለሁ፤ አገሬ አትፈርስም ከአገሬ በፊት ልጆቿ እንሞትላታለን ብለው ሥራቸውን አቁመው፣ እርሻቸውን ትተው፣ ቤተሰባቸውን በትነው በሞታቸው አገራቸውን አፅንተው ሊያቆሙ ዘምተዋል። መዝመት ያልቻሉት በደጀንነት ቆመው በስንቅና ትጥቅ ዝግጅቱ አጋርነታቸውን አረጋገጠዋል።

በውጭ አገር ያሉ ዲያስፖራዎችና የኢትዮጵያ ወዳጆች ሳይቀሩ በዲፕሎማሲው መስክ ተሰልፈው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እያሰሙ ናቸው ። ኢትዮጵያ እውነት አላት፤ ከኢትዮጵያ ላይ እጃችሁን አንሱ መልዕክታቸውን ለመላው ዓለም እያስተጋቡ ይገኛሉ። አሁንም ትግሉ በየአቅጣጫው ይቀጥላል።

ትግሉ አሁንም ተጠናክሮ ይቀጥላል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ የራሷን ሉዓላዊነት ታስከብራለችና። የራሷን ጉዳይ በራሷ የመፍታት የማይገሰስ መብትም አላት። ሉዓላዊት አገር ናት። ማንም ተነስቶ የሚያሽከረክራትና ማንም ተነስቶ ቁጭ ብድግ የሚያሰራው መሪ እንዲኖራት ከቶ አንፈቅድም። የጀግና ሰው ሞቱ ነው ክብሩ ብለናል።

በዚህ አገር መውደድ የጀግንነት ስሜት እና ወኔ ውስጥ ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የወሰዱት እርምጃም በዚያው ልክ ነው። ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ መሪዎች የመጡበትን የጀግንነት ታሪክ የሚደግም ነው። የወሰኑት ውሳኔና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች ያደረጉት ጥሪና ያስተላለፉት መልዕክት ታሪካዊና ወቅቱን ያዋጀ ነው። የዓድዋን ጀግንነት ለዘነጉ ምዕራባውያንንና አሜሪካኖች ታሪክን የሚያስታውስ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያውያን በምንከፍለው መሰዋዕትነት ልክ አገራችን ጸንታ ትቆማለች።

ለጥቁር ሕዝቦችም አርአያና የነጻነት ተምሳሌትነቷን አስጠብቃ ትኖራለች። ለዚህ ደግሞ የጀመርነውን የአገርን ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ሂደት ተጠናክሮ ይቀጥላል። ዛሬም ነገም ኢትዮጵያ በአገር ወዳድ ልጆቿ ታሸንፋለች!

አዲስ ዘመን  ኀዳር 23 / 2014

Recommended For You