በጦር ሜዳው የተገኘው ድል የኢኮኖሚ ጫናውን በማርገብም ይደገማል

ድልድይ አፍራሾቹ አሸባሪዎች ከአርባ ዓመት በፊት የነበረባቸው በሽታ ተነስቶባቸው ከግለሰብ እስከ የመንግሥት ንብረት ማውደሙን አጠናክረው ቀጥለውበታል።

ለእኛ የማትገዛ ኢትዮጵያ አትኖርም የሚለው አሸባሪው ሕወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች በየደረሱበት ንጹሐንን ከመግደል አልፈው እንስሳትንም ጭምር የሌላቸውን ማንነት በመስጠት ሲገድሉ ሰንብተው ነበር።

ሰሞኑን ደግሞ በመጡበት ፍጥነት ወደ ኋላ ማፈግፈግ ሲጀመሩ በየደረሱበት በንብረት ማውደሙ ላይ እየተረባረቡ ይገኛሉ። እንግዲህ ይህ ሁሉ ዘመቻ በአሸባሪው ስሌት ከአሜሪካና አውሮፓውያን ጫና ጋር ተደርቦ ኢኮኖሚው እንዲዳከም እና መንግሥት ከአቋሙ እንዲዛነፍ በማድረግ ለማንበርከክ በማሰብ ይመስላል።

የገጠመን ጦርነት ከጠላቶቻቸን ተፈጥሯዊ ባህሪ አንጻር በጦር ሜዳ ውሎ ተጋድሎ ብቻ ማሸነፍ መሞከር አስቸጋሪ ነው።

ለውጡ ከመጣ ጀምሮ በከተማ የመሸጉ ወያኔዎችና ባንዳ ተላላኪዎቻቸው ህዝቡን በኑሮ ውድነትና በዋጋ ንረት ተስፋ በማስቆረጥ ከመንግሥት ለማፋታት፤ እንዲሁም መንግሥትን በተገቢው መንገድ ግብር እንዳይሰበስብ በማድረግ አቅሙን ለማሽመድመድ ብዙ ሥራዎች የሠሩ ቢሆንም ውጤታማ ሳይሆኑ የውሃ ሽታ ሆነው ቀርተዋል።

ይልቁንም በሚገርም ሁኔታ በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ ኢኮኖሚው እያንሰራራ መሆኑን የሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች እየመሰከሩ ይገኛል። ከቀናት በፊት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳብራሩት፤ ካለፈው ዓመት አንስቶ እየተባባሰ የመጣው የዋጋ ግሽበት ዜጎችን በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉትን የሚጎዳ እንዳይሆን መንግሥት የራሱን ገቢ በመሰዋት ለማስተካከል ሲሠራ ቆይቷል። ወቅቱ መንግሥት ሲያደርግ የነበረው ድጎማ ለህዝብ ቅድሚያ መስጠት አስፈላጊ በመሆኑ እንጂ መንግሥት ራሱ በጣም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነበር።

የተሠራው ሥራ በትክክል ህዝቡ ዘንድ መድረሱን ለማረጋገጥም ባለሙያዎች ወረዳ ድረስ በመሄድ የሚቀርበው ስንዴና ዘይት በትክክል በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላለው ዜጋ መዳረሱን የመቆጣጠር ሥራ ሲሠሩ ነበር። በወቅቱ ለተከሰተው የዋጋ ግሽበት አንዱ ምክንያት የነበረውንና በአምራችና ተጠቃሚ መካከል ያለውን ድልድይ በመቁረጥ በቀጥታ አምራችና ሸማች ለማገናኘት የተሠራውም ሥራ ውጤታማ ሆኗል።

በዚህና በሌሎች የቁጥጥር ሥራዎችም ባለፉት ሁለት ወራት የዋጋ ግሽበቱ የሚጨምርበት ደረጃ እየቀነሰ ወደ መረጋጋት እየመጣ ይገኛል። በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጦርነት እየተካሄደና በርካታ የኢኮኖሚ አሻጥሮች እየተሠሩ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጣር መቻል ትልቅ ድል ነው። ነገር ግን በቋሚነት የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ አርሶ አደሩ ዘንድ ያለው መነቃቃት ከምንም በላይ ተስፋ ሰጪ ነው።

ሁሉም አርሶ አደር ሊባል በሚችል ደረጃ ጠቅላይ ሚኒስትሩ «ማንኛውም መሬት ጦም አይደር» ያሉት እየተተገበረ ይገኛል። ይህ ጅማሮ ውጤታማና ዘላቂ እንዲሆን ከመንግሥት በኩል አቅርቦትን በማሟላት ረገድና ገበያውን ጤናማ በማድረግ በኩል ብዙ የሚጠበቅ በመሆኑ እኛም ዓይናችንን ሳናነሳ የምንከታተለው ይሆናል ሲሉ ሚኒስትር ደኤታው ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ መሰረት መስቀሌ በበኩላቸው ባለፉት አራት ወራት ከሀገር ውስጥ ታክስ ሊሰበሰብ ከታቀደው ዘጠና ሰባት በመቶ ማስገባት ተችሏል። ይህም ካለፈው ዓመት አንጻር የዘጠኝ ነጥብ ሰባት ቢሊየን ጭማሪ ያሳየ ነው። በጉምሩክ ታክስ ረገድም በአራት ወራት ውስጥ ሰማኒያ ስድስት በመቶ ማከናወን ተችሏል። ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሰይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር ከስድስት ቢለየን ብር በላይ እድገት ያሳየ ነው። በአጠቃለይ ከአስራ ስድስት ቢሊየን ብር በላይ ተጨማሪ ገቢ መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን፤ እንደ አጠቃለይ ከእቅዱ ዘጠና ሁለት በመቶ ማሳካት ተችሏል።

የተለጠጠ እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም ወቅታዊ ሁኔታን በማገናዘብ ነበር። ይህ ደግሞ ከአንድ ክልል ሙሉ ለሙሉና በሌሎች በተወሰኑ ቦታዎች ግብር ሳይሰበሰብ የተፈጸመም ነው። ይህንንም ውጤት ለማስመዝገብ ያስቻለን አንደኛ፤ ሠራተኛው ከመደበኛ ሥራ በተጨማሪ በሀገራዊ ስሜት እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ በመቻሉ፤ ሁለተኛም ህብረተሰቡ ያለውን የሀገሩን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት በሐቅ ግብሩን በወቅቱ እንዲከፍል የተሠሩት ሥራዎች ውጤታማ በመሆናቸው መሆኑን አስቀምጠዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ከትናንት በስቲያ ደግሞ መንግሥት በልዩ ሁኔታ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀባቸው ቦታዎች የወሰደው ዕርምጃ ለወያኔ እኩይ ሴራ ሁነኛ ማምከኛ መንገድ ነው። ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ያስተላለፈው መመሪያ እንዳስቀመጠው «አሁን ባለው ሀገር የማዳን ግዳጅ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ይታወቃል።በዚህ ምክንያትም በአንዳንድ አካባቢዎች የሰዓት እላፊ ገደብ የተደረገ ቢሆንም በአምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ ገደቡን ተግባራዊ ማድረግ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ጫና ስለሚያሳድርና ኢንዱስትሪዎችንም ወደ ኪሣራ ስለሚያስገባቸው የተቀመጠው የሰዓት እላፊ ገደብ ለሁሉም አምራች ኢንዱስትሪዎች እንደማይመለከት ታውቆ፤ ኢንዱስትሪዎቹ አስፈላጊ የሆነ የራሳቸውን የጥበቃ ስርዓት ከወትሮው በተለየ መልኩ አጠናክረው መደበኛ ሥራቸውን በተለመደው ሁኔታ እንዲቀጥሉ እንዲደረግ የሚያሳስብ ነው፡፡» አዋጁ በሀገሪቱ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያስገባ በመሆኑ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ መሬት በማውረድና የተቻላቸውን ሁሉ በማድረግ ሊተገብሩት የሚገባ ነው።

በመሰረቱ በግንባር የተሰለፈው ሠራዊት ድልን እንዲቀዳጅ የሚያስችለው ከኋላው የተሰለፈው ህዝብ ደጀንነት ነው። በዚህ ረገድ እስከ ቅርብ ጊዜ ሲሠሩ የነበሩ ሥራዎች በኢትዮጵያዊነታችን እንድንኮራ ያደረጉን ናቸው።

በክልል ዘማቾች ወደ ግንባር ሲሄዱ የየአካባቢው ሰው ተራ ገብቶ የዘማች አርሶ አደሮችን ማሳ እየኮተኮተ እያረመ ሲንከባከብ ነበር። ማንም ሊረዳው እንደሚችለው የሀገራችን ኢኮኖሚ እንኳን ከንብረት አውዳሚ አሸባሪዎች ጋር ጦርነት ውስጥ ገብተን ይቅርና ድሮም ቢሆን የዜጎችን ጠንካራ ተሳትፎና እንቅስቃሴ የሚፈልግ ነው።

በመንግሥትና በአምራች ድርጅቶች የሚሠሩ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ብቻቸውን ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ ሊያመጡ አይችሉም። በመሆኑም ከእያንዳንዱ ዜጋ እንደ ሀገር የገጠመንን ችግር በመገንዘብ በየተሰማራበት መስክ ከሁሉም ጊዜ በላቀ ጠንካራ ሥራዎችን መሥራት የሚጠበቅበት ይሆናል።

ዛሬ ተረባርበን የምንሠራቸው ሥራዎች እንደ ሀገርና እንደ ህዝብ ትልልቅ ሁለት ፋይዳዎችን የሚያስገኙልን ናቸው። የመጀመሪያው በየደረሰበት ውድመት እያስከተለ ተስፋችንን ሊያጨልም የመጣውን ወራሪ ኃይል እንኳን ለኢኮኖሚ ጫና ለምንም የማንበገርና ጠንካራ አንድነት ያለን ህዝቦች መሆናችንን የምናሳይበት ነው።

ሁለተኛው ደግሞ በሚቀጥሉት ቀናት እንደ ንጋት ጮራ መከሰቱ በማይቀረው ድላችን ተወረው የነበሩ ቦታዎችን ነፃ ስናስወጣ ወገኖቻችንን ለመታደግ አቅም የሚፈጥርልን ይሆናል። በመሆኑም ሁላችንም ኢትዮጵያውያን በልማቱም መስክ በተጠናከረ መልኩ በመዝመት የሕወሓትን እና ተላላኪዎቻቸውን እኩይ ዓላማ ልናመክን ይገባናል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን  ኀዳር 23 / 2014

Recommended For You