የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ያላገናዘበውና ቆሞ ቀሩ የአሜሪካ አቋም !

ከድሮ እስከ ዘንድሮ ስለኢትዮጵያ ዕድገትም ሆነ ውድቀት ሲነሳ አብሮ ይወሳል፡፡ የታሪክና የፖለቲካ ማጠንጠኛ፤ የዲፕሎማሲ መቀየሻ፤ የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳለጫ ፤የወታደራዊ አቅም ማሳያ ተደርጎም ይወሰዳል።

ብዙዎችም ዓለምን የመቆጣጠሪያው ቁልፍ ቦታ እን ደሆነም ይስማሙበታል-ቀይባህርና አካባቢው፡፡ ቀይ ባህር ከደቡብ ሶርያ ተነስቶ በእስራኤልና ዮርዳኖስ፤ በሳይናኢ አቋርጦ ወደ ቃባ ሰላጤ ይገባና ኢትዮጵያን ለሁለት ሰንጥቆ በኬንያ በኩል እስከ ታንዛንያ የሚደርሰው የታላቁ ስምጥ ሸለቆ አካል ነው፡፡

የቀይ ባህር አካባቢ እንደሌሎች አካባቢዎች አንድ የተወሰነ የመልካአምድር አቀማመጥ ብቻ ሳይሆን ታሪክም፤ፖለቲካም፤ኢኮኖሚም፤ወታደራዊ አቅምም በአጠቃላይ ሁሉን ጸጋዎች አጣምሮ የያዘ ስፍራ ነው። አካባቢው ካለው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አንጻር የቀይ ባህርን አካባቢ መቆጣጠር መቻል ዓለምን በእጅ እንደማስገባት የሚቆጠር ነው፡፡

የቀይ ባህር አካባቢ ምሥራቅ አፍሪካንና መካከለኛው ምሥራቅን ከማገናኘቱም በላይ ወደ አውሮፓና አሜሪካ ለሚጫኑ ሸቀጦች ዋነኛ መተላለፊያ ነው፡፡ ቀይባህር በዓመት 5,000 ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ጨምሮ 50 ሺህ መርከቦች የሚተላለፉበትና 41 በመቶ ሸቀጦች የሚጓጓዙበት ቁልፍ አካባቢ ነው፡፡ በየዓመቱም እስከ 700 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ልውውጥ የሚካሄድበት ዋነኛ የንግድ ቀጣና ነው፡፡

ባለፉት 50 ዓመታት እስራኤልና አረቦች ቀይ ባህርን ተቆጣጥረው የበላይነታቸውን ለማረጋገጥ ሲጥሩ ቆይተዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አሜሪካ፤ቻይና፤ሩስያ፤ቱርክና ኢራንን የመሳሰሉ ሀገራት በአካካቢው ላይ የበላይነታቸውን ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡

በተለይም አካባቢውን በጦር አቅም ጭምር ለመቆጣጠር በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ከፍተኛ ዶላር በማውጣት የጦር ሰፈሮችን በመቋቋም አካባቢውን የውጥረት ማዕከል አድርገውታል፡፡ ይህን በሥጋት የሚያዩት ምዕራባዊያኑ ከወዲሁ በቀጣናው ተፅዕኖ ለማሳረፍ ከባድ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተዋል፡፡ በአጠቃላይ የኃያላኑ ፉክክር አስደማሚ ነው፡፡ ይህን ስትራቴጂካዊ ቦታ በዘላቂነት መቆጣጠር የሁሉም ሀገራት ህልም ነው፡፡

ህልሙ የሚፈታው ደግሞ በኢትዮጵያ መሆኑ አሜሪካንን ጨምሮ ሁሉም ሀገራት የተስማሙበት ይመስላል፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ እምብርት ነች፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ካሉ ሀገራት ከሁሉም ጋር ድንበር የምትጋራና ማዕከል የሆነች ኢትዮጵያ ብቻ ስትሆን በህዝብ ብዛትና በቆዳ ስፋትም የጎላ ድርሻ አላት፡፡ ኢትዮጵያ ጥንታዊ ሀገር ከመሆኗም በሻገር የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት ነች፡፡ ከአረቡ ዓለም ጋር የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ያላትና በአፍሪካ ሀገራትም ዘንድ እንደ አርአያ የምትወሰድ በመሆኑ በቀይባህር አካባቢ እንደ ድልድይ ትቆጠራለች፡፡ ስለዚህም በርካታ ሀገራት የቀይ ባህር እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር ኢትዮጵያን ዋነኛ ማዕከላቸው ማድረግ ይፈልጋሉ፡፡ ልዕለ ኃያሏ አሜሪካም ይህንኑ እውነታ ቀድማ በመረዳት ኢትዮጵያን እንደፈለገች የምትጠመዝዛት ሃገር ለማድረግ ስትጥር ቆይታለች፡፡

የኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነት እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1903 አካባቢ የተጀመረ እና ከ113 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም በተለይም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መገባደድ በኋላ አሜሪካ ዋነኛ አጋሮቼ ብላ ከመረጠቻቸው ሦስት የዓለም ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር አካባቢ ቁልፍ ሀገር መሆኗን የሚያመላክት ነው፡፡ ሆኖም የአጼ ኃይለስላሴ መንግሥት የፍልስጤም ነፃነት የሚደግፍ አቋም እስኪይዝ ድረስ ኢትዮጵያ የአሜሪካ ድጋፍ አልተለያትም ነበር፡፡ ከአጼው ውድቀት በኋላ ግን አሜሪካ ወዳጅነት ወደለየለት ጠላትነት ተቀየረ። ጭራሹኑ የሶማሌ ተስፋፊ ኃይል ኢትዮጵያን እንዲወር በርካታ ድጋፎችን አስከማድረግ ደረሰች።

ከጦርነቱ በኋላም በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት ፊቱን ወደ ሩስያ አዞረ፤ ሶሻሊዝምን መመርያው ማድረጉን አወጀ፤ በዚህም ከአሜሪካ ጋር ፈጽሞ ተቃቃረ፡፡ ላለፉት 50 ዓመታት በቀይ ባህርና አካባቢው የፈለጉትን ሲተክሉ፤ያልተስማማቸውን ሲነቅሉ የኖሩት አሜሪካኖች የደርግ ውሳኔ እንቅልፍ ነሳቸው። ማንኛውንም መስዋዕትነት በመክፈል የመንግሥቱ ኃይለማርያምን መንግሥት ለማስወገድ ቆረጡ፡፡ የተቀናጀ ስልት በመንደፍም በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም አመራር ላይ ዘመቱ፡፡ አሜሪካ የመንግሥቱ ኃይለማርያምን መንግሥት ለመጣል ከተጠቀመችባቸው ስልቶች አንዱ በሀገር ውስጥ ላሉ አማጽያን ያልተቆጠበ ድጋፍ ማድረግ ቀዳሚ ነበር፡፡

አሜሪካ በወቅቱ ለነበሩት ለሕወሓትና መሰሎቹ የሱዳንን ድንበር በመጠቀምም በገፍ መሳርያ አስገብታ ታስታጥቅ ነበር፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎት አይደርስባቸውም የሚባሉ አካባቢዎችን እንደሽፋን በመውሰድ በርዳታ ስም ከአየር መሳርያ ወደ መሬት ያቀብሉ ነበር፡፡ አልፎ ተርፎም የሳተላይት ድጋፍ በማድረግ ወታደሩ ለጥቃት እንዲመቻች ያደርጉ ነበር፡፡ ከወታደራዊ ዕገዛ ጎን ለጎንም በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ያልተቋረጠ በሚዲያ የማጥላላት ዘመቻ ያካሂዱ ነበር፡፡

ቪኦኤ፤ ቢቢሲና ሬውተርስን የመሳሰሉ ሚዲያዎች የወገንን ጦር አኮስሰው፤ የጠላትን ጦር አግዝፈው ያቀርቡ ነበር፡፡ የወገን ጦር በየግንባሩ በተደጋጋሚ እንደሚሸነፍ፤ ወደ ኋላ እንደሚያፈገፍግና የተዳከመ ጦር እንደሆነ አድርገው ያቀርቡ ነበር፡ ፡ አማጽያኑ ያልተቆጣጠሯቸውን ከተሞች ተቆጣ ጥረዋል በሚል ሀሰተኛ ምስሎችን ያሰራጫሉ፣ የሠራዊታቸውን ስብዕና በሚገነባ እና ሰላማዊውን ህዝብ በሚያሸብር ደረጃ አዲስ አበባ ተከባለች ከሚለው ጀምሮ የውጊያ ሄሊኮፕተር ጥለናል እስከሚለው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ይሳተፋሉ።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም በዕርዳታ ስም ከገቡ ድርጅቶችና ሰብአዊ መብት ተሟጋች ነን ከሚሉ አምሳያዎቻቸው ጋር በመቀናጀትም መንግሥት የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር በሚያደርገው የህግ ማስከበር ዘመቻ፣ በሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ በዘር ማጥፋት፣ ሠራዊቱን በአስገድዶ ደፋሪነት፣ በዘራፊነት ወዘተ በመክሰስ የኢትዮጵያን መንግሥት የማዋረድና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ተሰሚነት እንዳይኖረው የማድረግ ስልታዊ ሥራዎችን ይሠሩ ነበር። እግረ መንገዳቸውንም ሀገራት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና እንዲያደርጉ ይገፋፉ ነበር፡፡

የጸጥታው ምክር ቤት ሳይቀር በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያደርግ ከአንድም ሁለት ጊዜ እንዲሰበሰብ አድርገው ያለውጤት ተበትኗል፡፡ የተቀናጀ ዘመቻ በመክፈትም የኢትዮጵያ መሪ ሀገሩን ለቆ እንዲወጣና በሀገሪቱ ላይ ለደረሰው ጥፋት ሁሉ ምክንያት እንደሆነ አድርጎ እራሱን እንዲቆጥር ይገፋፉት ነበር፡፡ ይህንኑ ጉዳይ አስመልክተው ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ አብዮቱና ትዝታዬ በሚለው መጽሐፋቸው ላይ የሚከተለውን ጭብጥ አስቀምጠዋል፡፡

አሜሪካኖች በኢትዮጵያ ያለው ግጭት በሰላም እንዲፈታ በቅድሚያ መንግሥቱ ኃይለማርያም ከስልጣን መውረድ እንዳለበትይወተውቱ ነበር፡፡ ይህንኑ መሰረት አድርገውም ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ‹‹በአሜሪካኖች በኩል የማልፈለገው እኔ ነኝ ›› እያሉ በየስብሰባው ይናገሩ ነበር። በወቅቱ የአሜሪካ አስተዳደር ብሄራዊ ፀጥታ ምክር ቤት ዳይሬክተር በነበረው ግለሰብ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ከስልጣን ወርደው በዘመነ መንግሥታቸው ለተፈጸመው ወንጀል እንደማይጠየቁ ተገልጾላቸው በሚፈልጉት ሀገር እንዲኖሩ ተመቻቸላቸው፡፡ ለዚህም ዙምባቤም ተመራጭ ሆነች፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናትና አማጺ ቡድኖች በለንደን እያደረጉት ያለው ድርድር ሳይጠናቀቅም አደራዳሪውና የምሥራቅ አፍሪካ ልዩ ልዑክ የነበረው ኸርማን ኮህን በተደራዳሪ ወገኖች ስምምነት ላይ የተደረሰ በማስመሰል የኢህአዴግ ጦር አዲስ አበባ እንዲገባ መፈቀዱን መግለጫ ሰጠ፡፡ በሕወሓት የሚመራው ኢህአዴግ ሠራዊት በተነጠፈለት ቀይ ምንጣፍ ላይ እየተረማመደ አዲስ አበባ ገባ፡፡‹‹ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ሲልም ኢትዮጵያን መቆጣጠሩን›› አወጀ፡፡

በአሜሪካ አንቀልባ ታዝሎ አዲስ አበባ የገባውና በሕወሓት የበላይነት የሚዘወረው የኢህአዴግ መንግሥት ኢትዮጵያን የተቆጣጠረው ለህዝብ ጥቅም ሳይሆን ለራሱና ለአሜሪካ ጥቅም መሆኑ የታወቀበት ሳይውል ሳያድር ነው። የነፃነት ተምሳሌት፤ የቅኝ ገዢዎች የእግር እሳት፤የአፍሪካ ቀንድ ኮከብ የሆነችውን ኢትዮጵያን ለማዳከምና የውጭ ኃይሎችን ፍላጎት ለማሳካት ብሄር ተኮር የፖለቲካ ሥርዓት በኢትዮጵያ ምድር ተከለ፡፡

ብሄርን ከኢትዮጵያዊነት በላይ በማግነን ኢትዮጵያን ከከፍታዋ ለማውረድ ሞከረ፡ ለኢትዮጵያ ክብር የቆሙትንም በገፍ አሰረ፤አሰቃየ፤ገደለ። ሕወሓት ኢህአዴግ ሀገሪቱን ባስተዳደረባቸው 27 ዓመታትም በርካቶች ተሰደዱ፤የቀሩትም በየእስር ቤቱ ታጎሩ፤ ብዙሃኑም የበይ ተመልካች ሆኖ ቀረ፤ የሀገሪቱ ሀብትም በገፍ ተጋዘ፡፡ ኢትዮጵያም ርቃኗን ቀረች፡፡ በሕወሓት ኢህአዴግ አገዛዝ የተማረረው ህዝብም በአገዛዙ ላይ ማመጽ ጀመረ፡፡ በመጨረሻም ዘረኛውን የኢህአዴግ አስተዳደር አሽቀንጥሮ ጣለው፡፡ በምትኩም በዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሚመራ የለውጥ ኃይል ብቅ አለ፡፡ የለውጥ ኃይሉ በጥቂት ቀናትም ከውስጥም ከውጭም ድጋፍ አገኘ፡፡

በለውጡ ተስፋ ያደረገችው አሜሪካም ከአዲሱ መንግሥት ጎን መቆሟን አበሰረች። እስከ 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ድጋፍም አደረገች፡፡ ዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅትም የእርሷን ድጋፍ በመከተል ለለውጡ መንግሥት ድጋፍ አደረጉ፡፡ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም አብረው ዘመሩ፡፡ ሆኖም አሜሪካ እንደ ኢህአዴግ መንግሥት ተላላኪና ተንበርካኪ ይሆናል ብላ የጠበቀችው አዲሱ አስተዳደር ከአሜሪካ ይልቅ ህዝብንና ሀገርን አስቀደመ፡፡

ለእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ በሩን ዝግ አደረገ፡፡ ይባስ ብሎም በዶክተር ዐቢይ አሕመድ ፊት አውራሪነት ለሃያ ዓመታት በጠላትነት የዘለቀውን የኢትዮጵያና የኤርትራን ግንኙነት ሰላማዊ አደረገ፡፡ አልፎም ሶማሊያን የእርቁ አካል አደረገ፡፡ በሽኩቻ ውስጥ የነበሩትን የሰሜን ሱዳን ተቀናቃኞችን በሚያስገርም ፍጥነት አስማማ፡፡ የደቡብ ሱዳንን ተፋላሚዎችንም አቀራረበ፡፡ ኬንያ ሱማሊያም ልዩነታቸውን ፈትተው ስለልማት እንዲያወሩ መንገዱን ጠረገ፡፡ በአጠቃላይ በግጭትና በርሃብ ለሚታወቀው የምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ አዲስ ተስፋ ፈነጠቀ፡፡

እውቁ ፖለቲከኛ እንዳርጋቸው ጽጌ እንደሚናገሩትም ከአፍሪካ ቀንድ ግጭትና ሁከት ሲያተርፉ ለኖሩት አሜሪካና መሰሎቿ የዶክተር ዐቢይ በቀጠናው ላይ መከሰት በጣም አስደንጋጭ ነበር፡፡ የዶክተር ዐቢይ አመራር በአጭር ጊዜ የፈጸማቸው ሀገርና ህዝብን መሰረት ያደረጉ እንቅስቃሴዎች ብሎም የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን በማስተባበር ረገድ ያሳደረው ተጽዕኖና ተቀባይነት ውሎ ሲያድር ሙሉ አፍሪካን እንደሚያሳጣቸው ነጋሪ አላስፈለጋቸውም፡፡

በተለይም የህዳሴን ግድብን በተመለከተ አሜሪካ ያራመደችውን ግብፅን የወገነ አቋም እንዲቀበል በተደጋጋሚ የቀረበለትን ውሳኔ ሃሳብ አልቀበልም ማለቱ አሜሪካንን በተደፈርኩ ባይነት እንድትቆም አደረጋት፡፡ ስለሆነም ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ በአፍሪካ ቀንድ እየደመቀ የመጣውን መሪ ለማሰናከል አሜሪካ ቆርጣ ተነሳች፡፡ ኢትዮጵያና መሪዋን ለማዋረድና ለማንበርከክም በ1980ዎቹ የሄዱበትን መንገድ በመድገም አሸናፊነታቸውን ዳግም ለማረጋገጥ ተነሱ፡፡

የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምን መንግሥት የጣሉባቸውን ስልቶች እንደፍቱን መድሃኒት በመውሰድ አንድ በአንድ መተግበር ጀመሩ፡፡ ለተልዕኳቸውም የሚጋልቡትን ፈረስ ሲያፈላልጉ የትላንት ተላላኪያቸውን ከመቃብር አፋፍ ላይ አገኙት። አሸባሪው ሕወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 በመከላከያ ሠራዊት ላይ በፈጸመው ክህደት በራሱ ላይ ሞት ጋብዞ በአስራ አምስት ቀናት ውስጥ በደረሰበት ምት ወደ ሞት አፋፍ ተቃርቦ የነበረውን ቡድን እንደምንም ነፍስ ዘርተው አስነሱት። አሸባሪው ቡድን በበኩሉ ከገባበት ጨለማ ውስጥ እንደትላንቱ ልታወጣው የምትችለው አሜሪካ እንደሆነች አምኗል፡፡

በተለይም የዴሞክራቶች መመረጥ የበለጠ እንደሚጠቅመው በድብቅ ሾልኮ በወጣው ‹‹የትግል ልዩ ምዕራፍ እድገቶች እና የምከታችን ቀጣይ ስትራቴጂዎች፣ ስልቶች እና አቅጣጫዎች›› በሚለው ሰነድ ላይ በግልጽ ተመላክቷል፡፡ ስለሆነም በዚች ቁርጥ ሰዓት ጋላቢና ተጋላቢ ተገናኙ፡፡ እንደትላንቱም ሀገር የማፍረስ ዘመቻቸውን በይፋ አወጁ፡፡ እንደ ትላንቱም ዛሬ መጠነ ሰፊ በሆነ የሚዲያ ዘመቻ መንግሥት የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር በሚያደርገው የህግ ማስከበር ዘመቻ፣ በሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ በዘር ማጥፋት፣ ሰራዊቱን በአስገድዶ ደፋሪነት፣ በዘራፊነት ወዘተ የስም ማጥፋት ዘመቻ ከፈቱ፡፡ በዕርዳታ ስምም የመሳሪያና ሎጀስቲክ ድጋፍ ማድረግ ጀመሩ፡፡

የሳተላይት ድጋፍ ሳይቀር ለአማጺ ቡድኑ እያደረጉ ነው፡፡ እንደቀድሞ ሁሉ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ የኢትዮጵያን ስም የማጉደፍና ዲፕሎማሲያዊ ተቀባይነት እንዳይኖራት የማድረግ ዘመቻዎችም በስፋት በመሥራት ላይ ናቸው። አስራሁለት ጊዜ በጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ ጉዳይ መወያያ እንዲሆንና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያሳድር ብዙ ተሠርቷል፡፡

ሆኖም በትላንት በሬ ለማረስ የሚሞክሩት አሜሪካኖች የዛሬዋን ኢትዮጵያንም ሆነ ዓለም አቀፋዊውን ሁኔታ የተረዱት አይመስልም፡፡ ዛሬ ያለው የኢትዮጵያ የውስጥ ሁኔታም ሆነ አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ አሰላለፍ ከ1983 ጋር ፈጽሞ የተለያየ ነው፡፡ የቀዳማዊ ኃይለስላሴን መንግሥት ለመጣል የተቀጣጠለው ህዝባዊ አመጽ ፍሬ እንዲያፈራና ያረጀ ያፈጀው ስርዓት እንዲገረሰስ የወታደሩ ክፍል የማይተካ ሚና ተጫውቷል። ወታደሩን ወክሎ ወደ ስልጣን የመጣው የደርግ መንግሥትም በመጀመሪያዎቹ የስልጣኑ ዓመታት ሰፊ ተቀባይነት ነበረው። ሆኖም በሂደት ወታደራዊ ኃይሉ ኢህአፓና መኢሶንን ከመሳሰሉ የፖለቲካ ኃይሎች በገባው የቀይ ሽብር ነጭ ሽብር ደም አፋሳሽ ሽኩቻዎች ቀስ በቀስ ተቀባይነቱን እያጣ መጣ። በተለይም በከተሞች አካባቢ ቀይ ሽብር በሚል ዘመቻ ወታደራዊ ኃይሉ ከየቤቱ ወጣቶችን በገፍ እየለቀመ መረሸኑ በህዝብ እንዲጠላ አድርጎታል፡፡ በአርሶ አደሩም ዘንድ በመጀመሪያዎቹ አካባቢ መሬት ላራሹን በማወጅ ተቀባይነት ማግኘት ችሎ የነበረ ቢሆንም አርሶ አደሩ ምርቱን መንግሥት በወሰነለት ተመን እንዲሸጥ መገደዱ እንደከተማው ሁሉ የገጠሩም ህዝብ ልቡ እንዲሸፍት አድርጎታል፡፡

በመሆኑም በከተማም ሆነ በገጠር የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በደርግ መንግሥት ላይ ቂም በመቋጠሩ ስርዓቱን ለመጣል የሚደረጉ ትግሎችን በሙሉ ይደግፍ ነበር። ይህን አጋጣሚ እንደጥሩ ዕድል የቆጠሩት ሕወሓትና መሰል አማጽያን ራሳቸውን ቅዱስ ፤የደርግ መንግሥትን እርኩስ አድርገው ቀረቡ፡፡ መጥፎ አመላቸውን በጉያቸው ደብቀው የተጣላ አስታራቂ፤ ለእውነት መስካሪ፤ ለፍትህ ተሟጋች መስለው ታዩ፡፡

የደርግ መንግሥት አምባገነንነትና ጨፍጫፊነት ታክሎበት ህዝቡ በአማፅያኑ አስመሳይ ባህሪ ተታለለ፡፡ካለውም ላይ አየቀነሰ፤ ከማዐዱ እያቋደሰ ፤መሳሪያ እየተሸከመና መንገድ እየመራ አማፅያኑን ለስልጣን አበቃቸው፡፡ ሆኖም ክፉ አመልን ሸሽጎ ብዙ መጓዝ አይቻልምና መንበረ ስልጣኑን የተቆጣጠረው በሕወሓት የበላይነት የሚመራው ኢህአዴግ ህዝብና ሀገር ጠል ባህሪው ለመገለጥ ብዙ ጊዜ አለወሰደበትም፡፡

ሀገርን ማዋረድ ፤ህዝብን በብሄርና በኃይማኖት ከፋፍሎ ማናከስ፤ጥቂቶችን ተጠቃሚ አድርጎ ብዙሃንን የበይ ተመልካች ማድረግ፤በመንግሥት ደረጃ የሚታገዝ የዘረፋ ስርዓት መዘርጋት፤ለእውነት የቆሙትን በገፍ መግደል፤ማሰቃየትና አለፍ ሲልም ከአራዊት ጋር ማሰር የመሳሰሉት ባህርያቱ ሀገሪቱን በገዛባቸው 27 ዓመታት የተገለጡ እውነታዎች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የኢህአዴግ አገዛዝ ዘመን በአብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ የጨለማ ዘመን ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ ስለዚህም ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ የሕወሓትን እውነተኛ ባህሪ ተረድቷል፡፡

እንኳን እንደትላንቱ መሳሪያ ተሸክሞ መንገድ እየመራ አዲስ አበባ ሊያስገባው ቀርቶ በማንኛውም መልኩ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ህልውና እንዲኖረው ፍቃደኛ አይደለም፡፡ ሕወሓት ከኢትዮጵያ ምድር መጥፋት እንዳለበት ሁሉም አንድ አቋም ላይ ደርሷል፡፡ በ1980ዎቹ በነበረው ጦርነት ከየቤቱ በግድ ታፍሶ ወደ ጦር ግንባር ይዘምት የነበረው ወጣት ዛሬ በፍላጎትና በቁጭት በገፍ በመዝመት ላይ ይገኛል፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ሀገር ወዳድ መሪ ይሁኑ እንጂ አገዛዛቸው አምባገነን ባህሪ ነበረው፡፡ በህዝብም ይሁንታ አግኝተው ለመሪነት የበቁ አይደሉም።

የዛሬው የኢትዮጵያ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በምርጫ ህዝባዊ ተቀባይነትን ያገኘና በውስጥም በውጭም ያለው ኢትዮጵያዊ መሪዬ ብሎ በአንድ ድምፅ የሚቀበላቸው ናቸው፡፡ ለወትሮው መንግሥትን በመቃወም የሚታወቀው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ እንኳን በአምስት አህጉራት በ30 ከተሞች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ያለውን ድጋፍ በነቂስ ወጥቶ አሳይተዋል፡፡አንዳንድ ዲያስፖራ አባላትም የሞቀ ኑሯቸውን በመተው ግንባር ድረስ ዘልቀው አሸባሪ ቡድኑን በመፋለም ላይ ይገኛሉ። ስለሆነም አሁን ያለው ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ ያለው በመሆኑ በ1980ዎቹ እንደተደረገው ህዝብን በመንግሥት ላይ አነሳሰቶ ስልጣን በአቋራጭ መያዝ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ከዚህ ሁሉ በሻገር ኢትዮጵያውያን ከትላንቱ ተምረው በእናት ሀገራቸው ህልውና ላይ ጋራ አቋም ይዘዋል። ከልዩነት አንድነትን መርጠዋል፡፡

የዘር ፤የኃይማኖትና የፖለቲካ ልዩነት ሳይበግራቸው የኢትዮጵያን ህልውና ለማስከበር በጋራ ዘብ ቆመዋል፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ገዢው ፓርቲ በጋራ ሆነው ኢትዮጵያን ለማዳን ተሰልፈዋል፡፡ የዛሬው ትውልድ እንደ1980ዎቹ በወሬ የሚፈታ አይደለም፡፡ አማጽያን ይሄን ያህል ወታደር ማረኩ፤አዲስ አበባ ደረሱ፤ ሰማይ ወጡ መሬት ወረዱ በሚሉ ነጭ ውሸቶች ተረብሾ ሀገሩን ለሰርጎ ገቦችና ለባዕዳን አሳልፎ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ይልቁንም ትዊተርን በመሰሉ የማህበራዊ ሚዲያዎች በመጠቀም ነጭ ውሸቶችን ፀሐይ እንዲሞቃቸው እያደረገ ነው፡፡ ስለዚህም አንድም ጥይት ሳይተኩሱ በሃሰት የወሬ ጋጋታ አዲስ አበባ መሰስ ብሎ መግባት ፋሽኑ ያለፈበት ስልት ነው፡፡ ከህዝቡ አብራክ የወጣው መንግሥትም በሚዲያ ጫና የሚሸበር፤ በአሜሪካ ግፊት ሀገሩን ለቆ የሚሰደድ አይደለም።

ትላንት በነበረው ግፊትና የሚዲያ ዘመቻ ‹አንድ ጥይትና አንድ ሰው› እስኪቀር እዋጋለሁ ያሉትን መንግሥቱ ኃይለማርያምን ከሀገር እንዲወጡ ማድረግ ተችሎ ይሆናል። ዛሬ ግን ለየትኛውም ግፊት የማይንበረከክና የትኛውም የሚዲያ ጫና የማያሸብረው መሪ ተፈጥሯል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አዲስ ወግ በተሰኘው ፕሮግራም ላይ ተገኝተው ‹‹ እዚሁ በሀገሩ የሚሞት እንጂ የሚሰደድ መሪ የለም›› ሲሉ እንቅጩን ነግረዋቸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ቃላቸውን ግንባር ድረስ በመዝመት አረጋግጠዋል፡፡የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን መሪ መሆናቸውን አሳይተዋል፡፡

ህዝቡም የመሪውን ፈለግ ተከትሎ አሸባሪውን ሕወሓት ለመቅበር እየተመመ ነው፡፡ ስለሆነም እንደ1980ዎቹ መሪ አስኮብልሎ እየተንጎማለሉ አራት ኪሎ ቤተመንግሥት መግባት የህልም እንጀራ ነው፡፡ በ1980ዎቹ የነበረውን የኢትዮጵያ ህዝብ ሁኔታ ከአሁኑ ጋር ማነጻጸር እንደማይቻል ሁሉ አካባቢያዊና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችም እንዲሁ በእጅጉ የተራራቁ ናቸው፡፡ በ1980ዎቹ የነበረችው ኢትዮጵያ ድንበር ከምትጋራቸው ሀገራት በሙሉ ጤነኛ ግንኙነት አልበራትም፡፡

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ከኤርትራ ጋር ለ17 ዓመታት የዘለቀ የእርስ በእርስ ጦርነት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ የሱዳን መንግሥት ድንበሩን ሁሉ ክፍት በማድረግ ለአማጽያን ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ የሚያደርግ ነበር፡፡ ከሶማሌያ መንግሥት ጋር በወሰን ይገባኛል የለየለት ጦርነት ውስጥ ተገብቷል፡፡ የኬንያ መንግሥትም ቢሆን በርዕዮተ ዓለም ልዩነት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ እምነት አልነበረውም። በድንበር የማትዋሰነው ሊቢያ ሳትቀር በኢትዮጵያ ላይ ጦር ሰብቃለች፡፡ በአጠቃላይ የደርግ መንግሥት ከውስጥም ከውጭም በጠላት የተከበበ ባይተዋር መንግሥት ነበር፡፡

ይህ ደግሞ ሕወሓትን ለመሰሉ አማጽያን እና እንደ አሜሪካ ላሉ የውጭ ኃይሎች ዓላማቸውን በቀላሉ እንዲያሳኩ በር ከፍቶላቸዋል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን እየመራ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት ከቀጣናው ሀገራት ጋር መልካም ወዳጅነት ያለውና ተጽዕኖ ፈጣሪ ነው፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥም በግጭትና በርሃብ የሚታወቀውን የምሥራቅ አፍሪካን ቀጣናን በማስተባበር ወደ ሰላምና ልማት ያመጣ የአካባቢው ፈርጥ ነው፡፡

መስከረም 14 ቀን 2014 በተካሄደው የመንግሥት ምስረታ ላይ የተገኙት የኬኒያ፤ የሶማሊያ፤ የደቡብ ሱዳን፤የጅቡቲ፤የዩጋንዳ፤የናይጄሪያ መሪዎችም ያረጋገጡት ይህንኑ ሀቅ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ለ20 ዓመታት ያህል በግጭት ስጋት ውስጥ የነበሩትን ኢትዮጵያና ኤርትራን ወደ ሰላም በማምጣት ታሪክ ሰርተዋል፡፡ ለዚህ በጎ ሥራቸውም የዓለም የሰላም ኖቤል ተሸላሚ መሆን የቻሉ አንጸባራቂ መሪ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የዶክተር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ወዳጅ በሆኑ ሀገራት የተከበበና ኢትዮጵያንም ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከል ዘብ የሚቆሙ ጎረቤቶች ያሉት ነው፡፡ ስለሆነም ባይተዋር እንደነበረው እንደ በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ወቅት እንደተደረገው የቀጣናውን ሀገራት አሰልፎ መንግሥትን ለመገልበጥ የሚቻልበት አንዳችም ቀዳዳ የለም፡፡

ዓለም አቀፋዊ ሁኔታውም በእጅጉ የተለየ ነው። በ1980ዎቹ ዓለም በሁለት ጎራ የተከፈለች ነበረች፡ ሀገራት የነበራቸው አማራጭም በአንዱ ጎራ ስር መጠለል ነው፡፡ በወቅቱ የነበረው የደርግ መንግሥትም የሶሻሊዝምን ጎራ መርጦ ወዳጅነቱን በዋነኝነት ከሩስያ መንግሥት ጋር አድርጎ ቆየ፡፡ ሆኖም የሶሻሊዝም ስርዓት በሂደት እየተዳከመ መሄድ ከሩስያ የሚያገኘውን ድጋፍ አሳጣው፤ውድቀቱም ተፋጠነ። አሁን ያለችው ዓለም ከርዕዮተ ዓለም ጣጣ የተላቀቀችና በርካታ አማራጮችም ያሏት ነች፡፡በ1980ዎቹ ብቸኛ የዓለም መሪ የነበረችውን አሜሪካ ዛሬ በኢኮኖሚም ሆነ በወታደራዊ አቅም የሚገዳደሯት ሀገሮች ብቅ ብለዋል። ሀገራትም አማራጮችን አግኝተዋል፡፡

ቻይናን የመሳሰሉ ሀገራት በአፍሪካ በዓመት እስከ 200ቢሊዮን ዶላር በማፍሰስ አማራጭ ገበያ ፈጥረዋል፡፡ ቱርክ፤ ሩስያ፤ ህንድ ለየትኛውም ሀገር በራቸውን ክፍት አድርገዋል፡፡ ስለዚህም አዲሲቷ ኢትዮጵያ በበርካታ አማራጮች የተከበበች ነች፡፡ አሜሪካ በሯን ብትዘጋባት ሌሎች በሮችን አንኳኩታ ማስከፈት የምትችል ሀገር ነች፡፡ በአጠቃላይ አሜሪካ በ1980ዎቹ ውጤት ያመጣችባቸው መንገዶች ዛሬ መክነዋል፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ ከትላንቱ ተምሯል፡፡ ጎጂና ጠቃሚውን ለይቷል፡፡

አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችም ተቀይረዋል። ስለዚህም ትላንት የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም መንግሥት ለመጣል የጠቀሙ ዘዴዎች ዛሬ የዶክተር ዐቢይ አሕመድን መንግሥት ለመጣል አቅም የላቸውም፤ ዘመኑን የማይዋጁ ናቸው፡፡ በ1980ዎቹ የነበረው የጆርጅ ቡሽ አስተዳደር የደርግን መንግሥት በመጣል ቢያንስ የርዕዮተ ዓለም አሸናፊነትን ተጎናጽፏል፡፡ ዛሬ ያለው የባይደን አስተዳደር ግን ከራሱ ጥቅም ጋር በተጻራሪ የቆመ ይመስላል፡፡

የባይደን መንግሥት የኢትዮጵያን መንግሥት ለመጣል በሚል አሸባሪዎቹን ሕወሓትና ሸኔን በመደገፍ ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም የሸኔ ቡድን አይኤስ፤አይኤስን ከመሳሰሉ ዓለም አቀፍ የሽብር ቡድኖች ጋር በጥምረት በመሥራት ላይ እንደሚገኝ የተለያዩ መረጃዎች እየወጡ ባለበት በዚህ ወቅት አሜሪካ ከሸኔ ጎን መቆሟ ሰተት ብላ የሽብር ጎሬ ውስጥ እንድትገባ የሚያደርጋት ነው፡፡ በአጠቃላይ የባይደን አስተዳደር የኢትዮጵያ መንግሥትን ለማንበርከክ የመረጣቸው የትላንት ዘዴዎች ዛሬ ላይ የመከኑ ከመሆናቸውም ባሻገር በምሥራቅ አፍሪካ ሽብርተኝነት ስር እንዲሰድ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ አሜሪካ በራሷ ብሄራዊ ጥቅም ላይ በተጻራሪ እንድትቆም ያደርጋታል፡፡

ጥቅሶችና ማጣቀሻዎች

 1. መስፍን ወልደማርያም-አደጋ ያንዣበበበት አፍሪካ ቀንድ

 2. united states insetitute of peace

3. The Horn of Africa and the Gulf: Shifting pow[1]er plays in the Red Sea የተሰኘ ጥናት

 4.ገስጥ ተጫኔ የቀድሞ ጦር መጽሐፍ ደራሲ 5. ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ አብዮቱና ትዝታዬ

6. በምሥራቅ አፍሪካ አሜሪካ ልዩ ልዑክ ጄፍሪ ፊልትማን ከተናገሩት የተወሰደ

 7. ከአንጋፋው ፖለቲከኛ አንዳርጋቸው ጽጌ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ

 8. ታደሰ ቴሌ ሰልባኖ-ቅስም የሰበረው ርምጃ

9. ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ አብዮቱና ትዝታዬዬ

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን  ኀዳር 24 / 2014

Recommended For You