ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙ አጋር አገሮች ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ

አሸባሪው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ቡድን አሁንም መሽቶበት እንኳን ያልሞት ባይ ተጋዳይነቱን ቀጥሎበታል፡፡ በሰላም እጅ እንዲሰጥ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጥሪ ቢቀርብለትም ፈቃደኝነቱን ከማሳየት ይልቅ ጉድጓዱን አርቆ መቆፈር መርጧል፡፡ ቡድኑ እንዳሰበው ተሳክቶለት ቢሆን ኢትዮጵያ ዛሬ ፈራርሳ በታየች ነበር፡፡

በአንድነቱ የሚያምን ጽናት ያለው፣ ሰላም ወዳድ ህዝብ ያላት አገር መቼም እንደማትወድቅና እንደማትፈርስ አሸባሪውም ሆነ ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ሲወተውቱ የነበሩትም ሀቁን ላለመቀበል እንጂ ልባቸው ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡

አሜሪካና አንዳንድ የአውሮፓ አገራት ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ ለቀው እንዲወጡ ወትውተዋል። ወደ ኢትዮጵያ ዝር የሚል ዓለምአቀፍ ማህበረሰብ እንዳይኖር ጭምር ነበር ማስጠንቀቂያቸው፡፡ ጦርነቱ ከሚካሄድበት አካባቢ አልፎ አዲስ አበባ ከተማም የጦርነት አውድማ እንደምትሆን ዓይነት ነበር የዜጎች ለቃችሁ ውጡ ዘመቻው፡፡ ኢትዮጵያ ጦርነቱ ሲበረታባትና ኢኮኖሚያዋም ሲዳከም እጅ ትሰጣለች ነበር እሳቤው። ግን ያለሙት አልሆነም፡፡

ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዩዋን በራሷ መፍታትና መፍትሔ እንዳትሰጥ ጣልቃ በመግባት ብዙ ጥረት አድርገዋል ወጥተው ወርደው ሠርተዋል በማስፈራሪያ ጭምር ሽብር ሲነዙ ከርመዋል። መንግሥት ያሳየውን ትዕግስት ከሽንፈት በመቁጠር ብዙ ዕርምጃ ተጉዘዋል፡፡ ጦርነቱ እንዲባባስ አንዴ በሰብዓዊ ድጋፍ፣ ሌላጊዜ ደግሞ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ፣የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ብቻ ከሽብርተኛው ጎን ሆነው ያልሸረቡት ነገር የለም፡፡

ግን ሁሉም እንቅስቃሴያቸው ከሽፎባቸዋል፡፡ በተለይም ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ይደረግ የነበረው ውትወታ በመአድን ልማት፣ በግብርና ውጤቶች ማቀነባበር፣ የንግድና አገልግሎት ዘርፎች ላይ የተሰማሩ የተለያዩ የውጭ ኩባንያዎችም ከኢትዮጵያ እንዲወጡ የሚገፋፋ ጭምር ነው አካሄዳቸው፡፡ ግን ደግሞ ሀብቱን ያፈሰሰበትንና ትርፍ ያገኘበትን ለቆ ለመውጣት የሞከረም ብዙ የውጭ ኩባንያ አልታየም፡፡

ይልቁንም አጠናክሮ ለመቀጠል ቃል የገባና ሥራ ለመጀመር ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች መኖራቸው ነው እየታየ ያለው፡፡ ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙ ወዳጅ ሀገራት አጋርነታቸውን በማሳየት አሳፍረዋቸዋል፡፡

ከወዳጅ ሀገራት መካከልም በማአድን ዘርፉ ተሰማርተው በኢትዮጵያ በመንቀሳቀስ ላይ ከሚገኙ ሀገራት የእስራኤል የማእድን ኩባንያ ይጠቀሳል፡፡ ይኸው ዋና መስሪያ ቤቱን በእስራኤል ያደረገው ሌካ የተባለውና በማዕድን ዘርፍ የተሰማራው ኩባንያ የሥራ ኃላፊዎች ሰሞኑን ከማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ ጋር በሚኒስቴሩ መስሪያ ቤት ተገኝተው ምክክር ባደረጉበት ወቅት ኩባንያው ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጡን ከሚኒስቴሩ ማህበራዊ ድረገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በምክክሩ ወቅትም ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ‹‹በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አመራር መንግሥት ብልጽግናን በሀገራችን ለማስፈን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕርምጃዎችን በቁርጠኝነት ሲወስድ ቆይቷል፡፡

አገራችን በፈተና ላይ በምትገኝበት በዚህ ወቅት በግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ከፍተኛ ፋይዳ አለው፡፡ የእስራኤል የማዕድን ኩባንያዎች በዚህ ወሳኝ ወቅት ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ጎን ለእውነት ወግናችሁ ስለቆማችሁ ምስጋና ይገባቸኋል›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በምክክሩ ላይ የተገኙት በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ረታ ዓለሙ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ በማእድን ልማት ላይ የተሰማሩ የእስራኤል ማዕድን

ኩባንያዎች ተወካዮች በዘርፉ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን እንዲሁም የኩባንያዎቹ ኃላፊዎች በዚህ ወሳኝ ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን እንደሚቆሙና ሥራቸውንም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ማረጋገ ጣቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል፡፡ አምባሳደር ረታ ኢትዮጵያ እና እስራኤል ጠንካራ ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ትስስር ያላቸው መሆኑን በማስታወስ፣ የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ወዳጅነት ለማጠናከር ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚችል ነው የተናገሩት፡፡

በዚሁ ወቅት የማዕድን ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ሠራተኞች በወቅታዊና አገራዊ ጉዳይ ላይ ባደረጉት ውይይት ወቅቱ ትብብርን የሚጠይቅ እንደሆነና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሀገርን የማስቀጠል ዘመቻውን በመደገፍ ሀገራዊ ግዴታውን መወጣት እንዳለበት መግለጻቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡

ኢትዮጵያ ካለችበት ሁኔታና ኢኮኖሚዋን ከሚያዳክም ጫና እንድትወጣ ከመንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ የዜጎቿና የወዳጆቿም ያላሰለሰ የጋራ ጥረት እንደሚጠይቅ ነው በሚኒስቴሩ ከተካሄደው ውይይት መረዳት የሚቻለው፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ በተለያየ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ሥራቸውን እንዲቀጥሉና ዜጎችዋም ተረጋግተው እንዲኖሩ በኢትዮጵያ ላይ እምነቷን የጣለችው ቻይናም አጋርነቷን አሳይታለች፡፡ በተግባር የተደገፈ ድጋፏንም አረጋግጣለች፡፡

ረቡዕ እለት አዲስ አበባ ከተማ የገቡት የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዩ ኢትዮጵያ የውጭ ጣልቃገብነት ሳያስፈልጋት የራሷን ጉዳይ በራሷ መፍታት እንዳለባትም ተናግረዋል። በሴኔጋል በሚካሄደው ስምንተኛው የቻይና-አፍሪካ የሚኒስትሮች ምክርቤት ጉባኤ በሴኔጋል ዳካር ላይ ቻይና ለአፍሪካ የግብርና ምርቶች ከቀረጥ(ታሪፍ)ነፃ የገበያ ዕድል ለመስጠት መወሰኗንም አስታውቃለች፡፡

ቻይና የፈጠረችውን መልካም ዕድል፣ የማእድን ሀብቱን አሁን ካለው የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አያይዘው የምጣኔ ሀብትና የፖሊሲ ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በረኸተስፋ በሰጡት ትንታኔ፤ ኢትዮጵያ ባላት የመሬት ስፋትና የማእድን እምቅ ሀብት፣ የተማረና ጉልበት ያለው የሰው ኃይል ብዙ መሥራትና ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ያምናሉ። ኢትዮጵያ ጫና ውስጥ ሳትገባ ለኢኮኖሚ ትልቅ አውታር የሆኑ ሀብቶቿን የምትጠቀምበት ዕድል ያላት ሀገር ናት፡፡ ይሁን እንጂ እስከአሁን የወጪ ንግዷ በስፋት ትኩረት ያደረገው በቡና እና የቅባት እህሎች ላይ ነው፡፡

የማእድን ሀብቷ ግን ከእነዚህ ምርቶች ባልተናነሰ ገቢ የሚያስገኝ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ ነዳጅ ሲሆን፣ የወርቅና ሌሎች የመአድን ሀብቶችም ተጨማሪ ናቸው፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ ከምታወጣባቸው ዘርፎች አንዱ ነዳጅ በመሆኑ እዚህ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ቢሠራና ከዚህ ቀደም በዘርፉ የተጀመሩ ሥራዎች ቢጠናከሩ ብዙ ማትረፍ ይቻላል፡፡ በመሆኑም ማእድን ፍለጋ የሚመጡ ኢንቨስተሮች ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ፣ የመንግሥት የቁጥጥር ስልት ተለይቶና ታስቦበት ቢሠራ የተሻለ ይሆናል፡፡

ለአብነት ኢትዮጵያ ያላትን የነዳጅ ሀብት በቦታው ላይ ወደ ናፍጣና ወደ አውሮፕላን ነዳጅ መቀየር የሚቻልበት ቴክኖሎጂ ስላለ መጠቀም ይቻላል፡፡ እነዚህ ሀብቶች በሰላሙም ጊዜ ቢሆን በከፍተኛ ደረጃ የሚያስፈልጉ ናቸው፡፡ ማእድን በርከት ያለ መዋእለነዋይ ሊገኝበት የሚችል ሀብት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜም ነዳጅ፣ ወርቅ፣ አልማዝ፣ መዳብ በመሸጥ እየተጠቀሙ ያሉ ሀገራት በከፍተኛ ሀብት ላይ ነው የሚገኙት፡፡ ኢትዮጵያም ሀብቱ ስላላት ጥቅም ላይ በማዋል ከውጭ ምንዛሪ ጫና እንድትላቀቅ ያስፈልጋል፡፡

ይህ ሲሆን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን ምርት ማስቀረት ይቻላል፡፡ እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገለጻ፤ ጊዜው አሁን አፋጣኝ የሆነ ውሳኔ የሚሰጥበት ወቅት ነው፡፡ ምክንያቱም ሀገሪቱ በአንድ በኩል ህዝቧን መንከባከብ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በተለያየ መንገድ ለጦርነቱ የሚወጣውን ወጪ መተካት ይኖርበታል፡፡ ይህ ደግሞ በመንግሥት ላይ የሚጣል ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ከተለያዩ አካላት ተሳትፎ ይጠበቃል፡፡ ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙት ከ50 በላይ የሚሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች፣ በተለይም የፖሊሲ፣ የጂኦሎጂና ኢንቨስትመንት ጥናት የሚያካሂዱ በዚህ ወቅት ይፈለጋሉ፡፡ ሰፋ ያለ ውይይትና ምክክር ሲኖር መፍትሔና ውጤት ይገኛል። እንደነ አሜሪካ፣ሩሲያ፣አውሮፓ ህብረት፣ ጃፓን፣

ቻይና ያሉ አገራት ቲንክታንክስ የሚባሉ ሃሳብና ትችት የሚያቀርቡ የምርምር ተቋማት አሏቸው። ኢትዮጵያም እንደአስፈላጊነቱ እንዲህ ያለውን አሠራር በመከተል ጉዳዩ ሰፋ ባለ መልኩ እንዲታይና በመንግሥት ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ እንዳይቀር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በዓለምአቀፉ በኩል ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ ለማዳከም እየተደረገ ስላለው ጫና በተመለከተም ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በሰጡት ትንታኔ የሚያስፈራ ወይንም የሚያሰጋ ነገር የለም፡፡ አሜሪካ ኢትዮጵያ ከነፃ ገበያ ዕድል (ከአገዋ) እንድትወጣ በመሪዋ በኩል የተላለፈው ገና ውሳኔ አላገኘም፡፡ ጉዳዩ ለአሜሪካን ተወካዮች ምክርቤት ቀርቦ ለውሳኔ እተጠበቀ ነው። ውሳኔው ወይ ይወድቃል ወይንም ይፀድቃል፡፡

በመሆኑም ከወዲሁ ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም፡፡ አፍሪካ ፍሪ ኮንቲነታል ትሬድ ኤሪያ የሚባል ኢትዮጵያ መፈረሟ መዘንጋት የለበትም። ይህ የፊርማ ስምምነት ምርቶቻቸውን ያለቀረጥ ክፍያ ወደ ሌሎች አፍሪካ አገሮች መላክ የሚያስችል ዕድል ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ መታየት ያለበት ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በአገዋ ዕድል ተጠቅመው ምርቶቻቸውን ወደ አሜሪካን ሀገር በመላክ ይጠቀሙ የነበሩ እንደነ ባንግላዴሽ፣ ቬትናም ያሉ ሀገሮች በኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ቀውስ ምክንያት የሚልኩት የምርት መጠን እየቀነሰ ነው፡፡ ሀገራቱ የሚልኩት ምርት መቀነሱ ለኢትጵያ የገበያውን ዕድል ያሰፋላታል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ አምራቾች፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ዕድሉን መጠቀም ይችላሉ፡፡ በተጨማሪ ደግሞ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶችም የሚጠበቅባቸውን የዲፕሎማሲ ሥራቸውን በአግባቡ መወጣት ከቻሉ በተለያየ መንገድ እየተፈጠረ ያለው የኢኮኖሚ ጫና ስጋት ከንቱ ይሆናል፡፡ ከወደቻይና የተሰማው መልካም ብስራት ደግሞ ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ የሚያደርግ ነው።

በሴኔጋል በሚካሄደው ስምንተኛው የቻይና-አፍሪካ የሚኒስትሮች ምክርቤት ጉባኤ በሴኔጋል ዳካር ላይ ቻይና ለአፍሪካ የግብርና ምርቶች ከቀረጥ (ታሪፍ) ነፃ የገበያ ዕድል ለመስጠት መወሰኗን ነው፡፡ በገንዘብ ሲተመንም ከአፍሪካ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ወደ አገሪቱ የሚላከው ምርትም ወደ ሦስት መቶ ቢሊየን ዶላር ይገመታል፡፡ ቻይና የፈጠረችው ዕድል አገዋን ሊተካ የሚችል ትልቅ ትርጉም ያለው ነገር ነው። ከዚህ በኋላ እንደሀገር በትኩረት መሠራት ያለበት ኢንዱስትሪዎች በጥራትና በስፋት እንዲያመርቱ ማስቻልና ደንበኛ ተኮር ምርት እንዲያመርቱ ማድረግ ነው፡፡

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ እንዳሉት፤ በዓለምአቀፉ ከሰብዓዊ መብት ጋር ተያይዞ የሚነገረው ደግሞ በሂደት በዲፕሎማሲ የሚፈታ ጉዳይ ነው፡፡ በደፈናው የምዕራቡ የመገናኛ ብዙሃን እና አንዳንድ የመንግሥት ተወካዮች መግለጫ በሰጡ ቁጥር መደናገጥ ተገቢነት የሌለው ስጋት ነው፡፡ እውነቱን ይዞ እስኪገባቸው ማስረዳት ግን ይጠበቃል፡፡ አንረዳም ብለው ጽንፍ ከያዙ ደግሞ ጊዜ እየፈታው የሚሄድ ይሆናል፡፡

ትኩረቱ መሆን ያለበት ኢትዮጵያ ከገባችበት የተለያየ ጫና እንዴት መወጣት አለባት፣ በጫና ውስጥ ሆኖ የልማቱ ሥራ እንዴት መከናወን እንዳለበት፣ የወጪ ንግዱ ስለሚጠናከርበት፣ በጦርነት የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ስለማቋቋም ብቻ ነው ማሰብ የሚፈለገው፡፡ ጦርነቱ ሲያበቃ ደግሞ የዓለምአቀፉ ማህበረሰብ በራሱ በሰብዓዊ ዕርዳታና መልሶ በማቋቋም መሳተፋቸው አይቀርም፡፡ አሜሪካን ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር በዲፕሎማሲና በተለያየ መንገድ ግንኙነት ያላት ሀገር ናት፡፡

ኢትዮጵያ በየጊዜው በውስጥም በውጭም ፈተናዎች ቢገጥሟትም እንደወርቅ ተፈትና ፈተናዎችን በድል ትወጣለች፡፡ ጠላቶቿም አፍረው ወደመጡበት ይመለሳሉ፡፡ ዜጎቿ ዛሬ አንገታቸውን ቢደፉም በኢኮኖሚም ቢጎዱም በልማቱ ቀና ብለው የሚሄዱበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ የሁለም ዜጎቿ ተስፋ ነው፡፡

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን  ኀዳር 24 / 2014

Recommended For You