የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ክብር የሚጻረሩ እንቅስቃሴዎችን አወገዘ

• የኢትዮጵያን ወቅታዊ ጉዳይ በማስመልከት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ደብዳቤ ሊልክ መሆኑንም ገልጿል

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ችግር በመጠቀም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ክብር በመጻረር የሚያደርጉት አሉታዊ ተግባር የኢትዮጵያን ነባር ወዳጅነት የማይመጥንና የኢትዮጵያን ሕልውና የሚጋፋ ማናቸውም ድርጊት እንደሚያወግዝ ገለጸ፡፡ እየተደረጉ ያሉ አላስፈላጊ ጫናዎችን በመቃወም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ደብዳቤ ሊልክ መሆኑንም አስታውቋል፡፡


አሁን በአገራችን የተፈጠረው ግጭት ከመፈጠሩ በፊት ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ያስታወሰው የጉባኤው የአቋም መግለጫ፤ የሕወሓት ኃይሎች ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ጥረቱ ሳይሳካ ቀርቶ ወደ ጦርነት ተገብቷል፡፡


ኢትዮጵያና አጠቃላይም ቀጣናው ላይ ፍጎላት ያላቸው አንዳንድ ምዕራባውያን አገሮች ችግሩን ይበልጥ በማስፋትና በመለጠጥ ብሎም ባልተገባ መንገድ በመተርጎም አገሪቱ ላይ ከፍተኛ ጫና እያደረጉ ነው ብሏል፡፡


ምንም እንኳን የሃይማት ተቋማት ነፃና ገለልተኛ ቢሆኑም በአገር ሉአላዊነት ላይ ቀይ መስመር ስላላቸው አገራችንን በእጅ አዙር ለመግዛትና ለማንበርከክ ለሚፈልግ ኃይል መልዕክታችንን ማስተላለፍ እንፈልጋለን ብሏል በመግለጫው፡፡


አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነትና ሰብዓዊ ቀውሱን ሽፋን በማድረግ በአገራችን ላይ የሚያራምዱት የዲፕሎማሲና የሚዲያ ዘመቻ መኖሩን ያመለከተው ጉባኤው በመግለጫው፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያሳዩት አቋም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ያላገናዘበ፣ የአገርን ሉአላዊነትና ክብርንም የማይመጥን መሆኑንም አትቷል፡፡


ችግሩ ከአገራት ግንኙነትና ዲፕሎማሲ አንጻር የማይጠበቅ ቢሆንም በጉዳዩ ላይ ያለው እይታ በሂደት ይስተካከላል ተብሎ ቢጠበቅም ሊስተካከል እንዳልቻለ ያብራራው ጉባኤው በመግለጫው፤ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ያላቸው አቋምና የሚወስዱት ዕርምጃ ሆን ተብሎና ታስቦበት በሴራ ትንተና ላይ የተመሰረተ መሆኑንም አመላክቷል፡፡


አካባቢው ላይ ያላቸውን ጥቅምና ድብቅ ፍላጎት ለማሳካት ግልጽ ተጽዕኖ እየተፈጠረ መሆኑን ያስገነዘበው የተቋሙ መግለጫ፤ ተጨባጭ የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ዕርምጃዎች በማሳረፍ ወገንተኛ አቋማቸውን እያሳዩ ነው፡፡ ይህም ጦርነቱና አካባቢያዊ ቀውሱን ይበልጥ እንዲወሳሰብ ማድረጉንም አብራርቷል፡፡


በሌላ በኩል ደግሞ አገሪቱ ላይ እየሆነ ያለው ነገር በእጅጉ የሚያሳስባቸው፣ ብሔራዊ ጥቅማችን ሳይሸራረፍ ችግሩ በአገራችን አቅም ሊፈታ እንደሚችል በማመን የሚደግፉን ወዳጅ አገራት መኖራቸውን ያስታወሰው የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፤ ለሚደግፉንና እያገዙን ላሉ አገራት ለድጋፋቸው እውቅና ይሰጣል፡፡ ድጋፋቸውም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል፡፡


በአንጻሩ በዲፕሎማሲም ሆነ በሰብዓዊነት ሽፋን ወቅታዊ ችግርን በማወሳሰብ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ክብር በመጻረር የሚያደርጉት አሉታዊ ተግባር የኢትዮጵያን ነባር ወዳጅነት የማይመጥንና የኢትዮጵያን ሕልውና የሚጋፋ ማናቸውም ተግባር ላይ የተሰማሩ መንግሥታትም ሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንቅስቃሴ እንደሚያወግዝ አስታውቋል፡፡


ወቅታዊ የኢትዮጵያን ሁኔታ ምክንያት በማድረግ የተላለፈ የአቋም መግለጫና ዓለም አቀፍ ጥሪ በሚል ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚላከው ደብዳቤ በተለያዩ ቋንቋዎች መዘጋጀቱንና ለአገራት፣ ኤምባሲዎች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ሲቪል ማህበራት እንደሚላክ ተገልጿል፡፡


ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ህዳር 25 ቀን 2014 ዓ.ም

Recommended For You