‹‹ተማሪዎቼን ተሰናብቼ፤ የፒኤችዲ ጥናቴንም አቋርጬ ዘምቻለሁ›› -አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን


አዲስ አበባ፡- ትምህርትም ሆነ ሥራ የሚኖረው አገር ስትኖር በሚል የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎቻቸውን ተሰናብተውና የጀመሩትን የፒኤችዲ ጥናት አቋርጠው ወደ ግንባር ለመዝመት መወሰናቸውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን ገለጹ፡፡


አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ላይ የተጋረጠውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ኢትዮጵያውያን ከዳር ዳር እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ ትምህርትም ሆነ ሥራ የሚኖረው አገር ስትኖር በመሆኑ እኔም የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎቼን ተሰናብቼና የጀመሩትን የፒኤችዲ ጥናት አቋርጬ ወደ ግንባር ለመዝመት ወስኛለሁ ብለዋል፡፡


ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር በመዝመት ጦሩን ለመምራት የወሰዱት ዕርምጃ የኢትዮጵያውያንን ነባር ልማድና ባህል ወደፊት ያመጣ ነው ያሉት መምህሩ፤ በተለያዩ ዘመናት ኢትዮጵያ አደጋ ሲጋረጥባት መሪዎች የሚደበቁና የሚሸሹ አይደሉም፡፡ ከዚህ ይልቅ ግንባር ድረስ ዘምተው ከሚመሩት ሕዝብ ጋር የሚጋፈጡ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የወሰዱት ዕርምጃም የኢትዮጵያን የቆየና የዳበረ የሥነ- ልቦና የበላይነት የሚያስመሰክር ነው፡፡

የምንሳሳለትና እጃችን ላይ አለ የምንለውን ነገር ሁሉ የምንጠቀምበትና የምናጌጥበት አገር ስትኖር ነው ያሉት አርክቴክት ዮሐንስ፤ ኢትዮጵያ ላይ የተደቀነው የህልውና አደጋ ፋታ የማይሰጥ በመሆኑ ዜጎች የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው አገራቸውን ለማዳን ሊረባረቡ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡


እንደ አርክቴክት ዮሐንስ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው ዘመቻ የአፈሙዝ ብቻ አይደለም፡፡ በመሆኑም የተከፈተብንን የሚዲያዎችን የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ጨምሮ ልዩ ልዩ መልክ ያለውን አደጋ ለመቀልበስ እያንዳንዱ ዜጋ ራሱን የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወታደር አድርጎ ማየት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡


ሁሉም ዜጋ በአንድ ጊዜ ወደ ግንባር ሊዘምት እንደማይችል ያመለከቱት ምሁሩ፤ የአካባቢውን ፀጥታ በማስጠበቅ፣ ደጀን ሆኖ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ለመከላከያ ሠራዊቱ በመደገፍ፣ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን በማገዝና ሰርጎ ገቦችን በመቆጣጠር ለዘመቻው የድርሻውን የማይተካ ሚና ሊወጣ እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡


ዛሬ ላይ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ተንቀሳቅሰን የጠላቶቻችንን ፍላጎት በማምከን የኢትዮጵያን ህልውና የማስቀጠል ትልቅ ኃላፊነት እጃችን ላይ መውደቁን ጠቅሰው፤ ይህንን ጦርነት በድል መወጣት ታሪክ በደማቅ ወርቅ ቀለም የሚጽፈው የዚህ ትውልድ ትልቅ የታሪክ አጋጣሚ ነው ብለዋል፡፡


ስለሆነም ኢትዮጵያ የደረሰባትን የህልውና አደጋ እጅ ለእጅ ተያይዘን ቀለበስነው ብለን ነገ ለልጅ ልጆቻችን የምንነግረውና የምንጽፈው ታሪክ እንዲመዘገብ ኢትዮጵያውያን ከፍ ያለ ትኩረት ሰጥተው አሸባሪ ቡድኑን ለመቅበር የሚያደርጉትን ርብርብ እንዲያጠናክሩ የአደራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ህዳር 25 ቀን 2014 ዓ.ም

Recommended For You