የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር ቤት ለአገር መከላከያ ሠራዊትና ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር ለአገር መከላከያ ሠራዊት የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገለጸ:: የቴአትር ቤቱ አርቲስቶችና ሠራተኞች አሸባሪው ሕወሓት በከፈተው ጦርነት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል ቁሳቁስና አልባሳት የማሰባሰብ ሥራ መሥራታቸውንም ተመልክቷል::

የቴአትር ቤቱ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ወይዘሮ ኩሪ አየለ ትናንት በቴአትር ቤቱ በተካሄደ የርክክብ መርሀ ግብር ላይ እንደገለጹት፤ ቴአትር ቤቱ ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ ጦርነት የከፈተውን አሸባሪውን የሕውሓት ቡድን እየተፋለመና ድል እየተቀዳጀ ላለው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት አንድ ሚሊዮን ብር አበርክቷል:: ከ400 ኪሎ በላይ ዳቦ ቆሎም ለሠራዊቱ እያዘጋጀ ነው::

ቴአትር ቤቱ ለመከላከያ ሠራዊት ከለገሰው ጥሬ ብር በተጨማሪ ከ400 ኪሎ በላይ ለስንቅ የሚሆን ዳቦ ቆሎ እንዳዘጋጀ የጠቆሙት ዳይሬክተሯ፤ የሽብር ቡድኑ በፈጸመው ወረራ ምክንያትም ከቤታቸው ለተፈናቀሉት ወገኖችም ከሁለት መቶ ሺህ ብር በላይ የሚገመት አልባሳት መሰባሰቡንም ጠቁመዋል::

 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር ቤት አርቲስቶችና ሠራተኞች አማካኝነት በአሸባሪው ሕወሓት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፋነቀሉ ወገኖች የሚውል ቁሳቁስና አልባሳት የማሰባሰብ እንዲሁም ስንቅ  የማሰናዳት ሥራም መሠራቱን ገልጸዋል::

እንደ ወይዘሮ ኩሪ ገለጻ፤እስከአሁን ድረስ ለተፈናቀሉ ዜጎች ሃምሳ ፍራሽና ሃምሳ ብርድ ልብስ ተሰብስቧል:: ቴአትር ቤቱ በግብርና ሥራ ለሚተዳደሩና ወደ ግንባር ለዘመቱ አርሶ አደሮችም የደረሰ ሰብላቸውን የመሰብሰብ ሥራ ይሠራል:: በቀጣይም ለመከላከያ ሠራዊትና ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎችም የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል::

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር ቤት ሠራተኞች ለወገን ጦር ቀጥተኛ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ የጠቆሙት ወይዘሮ ኩሪ ፤ አገራቸውን ከጠላት ለመታደግም 10 የቴአትር ቤቱ ሠራተኞች በፍቃደኝነት መዝመታቸውንም አውስተዋል::

ቴአትር ቤቱ ኢትዮጵያ በሽብርተኛው የሕወሓት ቡድን አስገዳጅነት ጦርነት ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ ግንባር ድረስ በመገኘት ለወገን ጦር የስነ ጥበብ ሥራዎችን በማቅረብ ከማበረታታት ጀምሮ የስንቅና ሌሎች ድጋፎችን ለጀግናው መከላከያ ሠራዊት ሲያደርግ መቆቱንም አውስተዋል::

ዳግማዊት ግርማ

አዲስ ዘመን ኅዳር 25/2014

Recommended For You