የመላው አፍሪካ የንግድ ትርዒት ቀጣናዊ ትስስርን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ተገለጸ

አዲስ አበባ፡- የመላው አፍሪካ የቆዳ ትርዒት እና የፋሽን ምንጭ ሳምንት ኤግዚቢሽን የአፍሪካን የኢኮኖሚ ውህደትን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ተገለጸ::

ሰባተኛው የመላው አፍሪካ የቆዳ ትርዒት እና የፋሽን ሳምንት ኤግዚቢሽን ትናንት በስካይላይት ሆቴል በተከፈተበት ወቅት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሺሰማ ገብረሥላሴ እንደገለጹት፣ ጤናማ የአፍሪካ የንግድ ሰርዓት ሲፈጠር በኢኮኖሚ ያደገች አፍሪካን ለመፍጠር ያግዛል::

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ‹‹ዘመቻ ለህብረ ብሄራዊነት›› በማለት በአሸበሪው የሕወሓት ቡድን የተከፈተባትን ጦርነት በአስተማማኝ ሁኔታ ጠላቶቿን እያሳፈረች ትገኛለች ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ኢትዮጵያ ወንድማማችነትን የምትፈልግ የሌሎችን አገራት ሉአላዊነት የምታከበር ናት ብለዋል።

እንደ አቶ ሺሰማ ገለጻ፤ የምዕራባውያን አገራትና ሚዲያዎቻቸው በኢትዮጵያ ላይ የተዛባ መረጃ በማሰራጨትና ጣልቃ ለመግባት እየሞከሩ ይገኛሉ:: ኢትዮጵያ አሁን እያደረገች ያለው ጦርነት የመላ አፍሪካውያን ጦርነት በመሆኑ አፍሪካውያንና ወዳጆቿ ከጎኗ መሆናቸውን ‹‹የ #NO MORE ›› ንቅናቄን በመቀላቀል አጋርነታቸውን እያሳዩ ናቸው ብለዋል::

ወቅቱ ወንድማማችነትን፣ ጥንካሬንና የኢኮኖሚ ውህደትን፣ ዘርፈ ብዙ የንግድ እንቅስቃሴን የምናጎለበት በመሆኑ የመላው አፍሪካ የቆዳ ትርዒት እና የፋሽን ምንጭ ሳምንት ኤግዚቢሽን ቀጣናዊ የንግድ ትስስርን ያጎለብታል ብለዋል::

የዋሊያ ቆዳና ጫማ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ አለማየሁ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ማህበር የውጭ ምንዛሬ በማፍራትና በማዳን በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በሌሎች ዘርፎች ዕድገትና ልማት ማስመዝገብ የሚችል ነው:: ነገር ግን ዘርፉ ካለው እምቅ አቅም አንጻር አለማደጉና ተገቢውን ሚና ካለመጫወቱም ባሻገር አገር በቀሉ ባለሀብት የህልውና አደጋ ገጥሞታል ብለዋል::

እንደ አቶ ያሬድ ገለጻ፤ በዘርፉ በተሰማሩ አገር በቀልና በውጭ ባለሃብቶች በቂ ትብብር አለመኖር፣ ያልተገባ ውድድር መኖሩ ለዘርፉ አለማደግ ማነቆ ሆኗል:: የሚካሄደው ኤግዚቢሽን የአፍሪካን የኢንቨስትመንት አቅም ለማሳየትና ተጨማሪ ኢንቨስትሮችን ለመሳብ የሚያስችልና ችግሮቹን ለመቅረፍ አጋዥ ነው ብለዋል።

የቆዳው ዘርፍ በአግባቡ ከተመራ ለአስር ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ያስችላል ያሉት አቶ ያሬድ የአፍሪካን የንግድ እንቅስቃሴ ለማሳደግና የሚታሰበውን የኢኮኖሚ ውህደት እውን ለማድረግ በትብብር መሥራትና መደጋገፍ ወሳኝ ነው:: ስለዚህ የንግድ ሚኒስቴርና አጋር አካላት ለዘርፉ ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል አቶ ያሬድ::

በኤግዚቢሽኑ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ፣የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ልማት ኢንስቲትዩት ፕሬዚዳንቶች፣ የተባብሩት መንግሥታት የንግድ ድርጅት የአፍሪካ ተወካይና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

ሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን ኅዳር 25/2014

Recommended For You