አሸባሪው ሕወሓት ከዚህ በኋላ ለወረራ የገቡ ጀሌዎቹን የሚያድንበት አቅም የለውም ሲል ዕዙ አስታወቀ

አዲስ አበባ፡- አሸባሪውየ ሕወሓት ቡድን ከዚህ በኋላ ለወረራ የገቡ ጀሌዎቹን የሚያድንበት አቅም እንደሌለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ አስታወቀ። ባለፉት ሁለት ተከታታይ ቀናት በተደረገው ዘመቻ በሸዋ ፣ በጋሸና እና በወረኢሉ ግንባሮች ተጨማሪ ቦታዎች ከወራሪው ቡድን ነፃ መውጣታቸውን ዕዙ ገልጹዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ትናንት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ለወረራ የገባውን ጀሌውን የሚያድንበት አቅም አጥቷል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው የፀጥታ ኃይሎች የጋራ ጥምረት በሚወስደው ዕርምጃ በርካታ ቦታዎች ከአሸባሪው ቡድን ነፃ ወጥተዋል።

የፀጥታ ኃይሉ የጋራ ጥምረት በ‹ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት› ወደ ተወረሩት አካባቢዎች በጥልቀት በመግባት፣ አሸባሪው ሕወሓት ትጥቁን፣ ስንቁን፣ ኃይሉንና ጀሌውን እንዲሁም የዘረፈውን ንብረት ይዞ እንዳይወጣ እያደረገ ይገኛል፡፡ እጅ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነውንም እየደመሰሰው እንደሚገኝ በመግለጫው አመልክቷል።

ወደ ተወረሩ አካባቢዎች የገባው የአሸባሪው ሕወሓት ጀሌ ሁሉም የመውጫ በሮች ተዘግተውበታል ያለው መግለጫው፤ በተወረሩት አካባቢዎች የጸጥታ ኃይሎች የጋራ ጥምረት ባካሄዱት ዘመቻ በሺዎች የሚቆጠሩ የአሸባሪው ሕወሓት ጀሌዎች እጃቸውን እየሰጡ መሆኑ ተገልጿል።

ወራሪው ኃይል በከንቱ ያሰለፋችሁ ወጣቶች ከዚህ በኋላ ማምለጫ እንደሌላችሁ ተገንዝባችሁ እጃችሁን ለፀጥታ አካላት በመስጠት ራሳችሁን እንድታድኑ ሲል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ አሳስቧል።

ባለፉት ሁለት ተከታታይ ቀናት በተደረገው ዘመቻ በሸዋ ግንባር የቀወት ወረዳ፣ ለምለም አምባ፣ ጀውሐ፣ ሰንበቴ፣ አጣየ እና ካራ ቆሬ ከተሞችና አካባቢዎች ከወራሪው ኃይል ነፃ ወጥተዋል፡፡ በጋሸና ግንባር ደግሞ ኮን እና ዳውንት ሙሉ በሙሉ ከአሸባሪው ጸድተዋል፡፡ በወረኢሉ ግንባር ልጓማ ከተማ ነፃ መወጥቷን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ አስታውቋል፡፡

አሸባሪው ሕወሓት ለሰው ልጅ ኑሮና ለሰብዓዊ መብት የማይጨነቅ፤ የዕድገትና ለሥልጣኔ ፀርመሆኑን በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በገሃድ አሳይቷል፡፡ ማኅበራዊ ተቋማትን አፈራርሶና አውድሞ፣ የግለሰቦችን ንብረት በመዝረፍ፣ የየአካባቢውን ነዋሪዎች ረሽኖ፣ ሴቶችን ደፍሮና በሕፃናት ላይ አሰቃቂ ጉዳት አድርሶ በሰው ልጅ ላይ ተፈጽሞ የማያውቅ ከባድ ወንጀል ፈጽሟል ሲል ዕዙ አስታውቋል።

የሃይማኖት ቦታዎችን አርክሷል፤ አውድሟል፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን አቃጥሏል፡፡ ታሪካዊ ቦታዎችንና ቅርሶችን አፈራርሷል፡፡ በመሆኑም ይሄን የጥፋት ተግባር ለሰዎች መብት የሚታገሉ ሁሉ ሊያወግዙት ይገባል ሲል ጠይቋል።

የየአካባቢው የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች፣ በየጢሻው የገባውን የአሸባሪ የሕወሓት ጀሌ እጁን በሰላም እንዲሰጥ የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ያሳሰበው መንግሥት፣ ኅብረተሰቡም በየአካባቢው የተበተነውን የአሸባሪውን የሕወሓት ጀሌ ተደራጅቶ በመማረክ፣ የነፍስ ወከፍ መሣሪያውን እንዲታጠቅ፣ የቡድንና ሌሎች መሣሪያዎችን ደግሞ ለጸጥታ አካላት እንዲያስረክብ በድጋሚ ጥሪ አቅርቧል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት ነፃ ያልወጡ አካባቢዎችን በተሟላ መልኩ ነፃ ለማውጣት በተጋድሎ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህም አልፎ ሁላችንም ተባብረን አሸባሪው ኃይል ዳግም የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ፈተና እንዳይሆን ማድረግ ይጠበቅብናል ሲል ዕዙ በመግለጫው አስታውቋል።

ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የህልውና ዘመቻው መዳረሻ አሸባሪው ሕወሓት ዳግም የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ፈተና እንዳይሆን ማድረግ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ኅብረተሰቡ የጀመረውን ሁለንተናዊ ድጋፍ እስከመጨረሻው አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል ሲልም ዕዙ አስታውቋል።

የመከላከያ ኃይላችንን በሰው ኃይል፣ በአደረጃጀትና በትጥቅ ዐቅም አጠናክረን በማንኛውም ወገን የሚታፈርና የሚከበር መከላከያ ኃይል መገንባት እንደሚያስፈልግ የገለጸው ዕዙ፤ ወጣቶችም መከላከያን በመቀላቀል አገራቸው መቼምና በማንም የማትደፈር የማድረግ ታሪካዊ አደራ እንዳለባቸው በመግለጫው አሳስቧል። ሕዝቡም የጀመረውን ድጋፍ ከበፊቱ በተሻለ መንገድ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገልጿል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ኅዳር 25/2014

Recommended For You