የባንዳነት መጨረሻው ሁሌም ውርደት እና ሽንፈት ነው!

የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ሆነና፤ ኢትዮጵያ እልፍ ጀግኖችን ያፈራች አገር ብትሆንም፤ ጥቂት የእናት ጡት ነካሽና የበሉበትን ወጪት ሰባሪዎች የሆኑ አጎብዳጅ ባንዳዎችንም ማህጸኗ አፍርቷል፡፡ ትናንት ለአገርና ህዝባቸው ሲሉ ታላቅ ተጋድሎን ያደረጉ፤ ታላቅ ጀብድም የሰሩ፤ ስለአገርና ሕዝብ ሲሉ ታሪክ የማይዘነጋውን ሕያው መስዋዕትነት የተቀበሉ እንደ እነ አፄ ዮሓንስ፣ አጼ ቴዎድሮስ፣ አፄ ምኒልክ፣ በላይ ዘለቀ፣ ባልቻ አባ ሳፎ፣ አብዲሳ አጋ፣ ጃጋማ ኬሎ፣ ዘርዓይ ደረስ እና ሌሎችም አያሌ ጀግኖች በበቀሉባት አገረ ኢትዮጵያ፤ አገርና ሕዝባቸውን ረስተው ለሆዳቸው ሲሉ አገራቸውን አሳልፈው የሸጡ፤ ለባዕዳን ተላላኪ በመሆን ኢትዮጰያን የወጉና ኢትዮጵያውያንን ያደሙ ኃይሎችም በቅለውባታል፡፡

የትም ይሁን የት ባንዳዎች አገርና ሕዝብ ውለታና ጀግንነታቸውን ከማይዘነጋቸው አያሌ አርበኞች በተቃራኒው፤ በስራቸው ትውልድ የሚያፍርባቸው፣ ምግባራቸው በከፋ ታሪክ የሚጻፍ፣ በአጎብዳጅ ተላላኪነታቸው ባዕዳን ጭምር የሚዘባበቱባቸው የትውልድ አተላ ሆነው የሚገለጹ በቁም የሞቱ የታሪክ ዝቃጮች ናቸው፡፡ አሸባሪዎቹ ሕወሓት እና ሸኔ ደግሞ የዚህ የከፋ ምግባር መገለጫ፤ የታሪክ አተላነት መታወሻ፤ ስለ ሆዳቸው ሲሉ አገርና ሕዝባቸውን የወጉ ባንዳዎች ሆነው በቀዳሚነት የሚገለጹ የዘመኑ የእናት ጡት ነካሾች፤ የበሉበትን ወጪት ረጋጮች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያን እያደሙ ያሉት የዛሬዎቹ ባንዳዎች ትናንት በጫካ ሲፈለፈሉ የብሔር ካባን ደርበው፣ የውጭ ኃይሎችን አጀንዳ አንግበው ነበር፡፡ ዛሬም ይሄው ባህሪያቸው አብሯቸው አርጅቶ እየሞተ፤ ጉድጓዱ ተምሶም ቀብሩ ሊፈጸም እየተዘጋጀ ይገኛል፡፡ ትናንት በዓድዋ አያቶቻቸው የኢትዮጵያን አርበኞች ተፋልመው ማሸነፍ ተስኗቸው የቅኝ ግዛት ህልማቸው የጨለመባቸው አገራትና መንግስታት እንደፈለጉ የሚጋልቧቸው ሆድ አደር መሆናቸው ደግሞ ለውርደታቸው መፋጠን ምክንያት ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ለባንዳ ቦታ የላቸውምና ነው፡፡ ባንዳነትን እጅግ አብዝተው የሚጠየፉት እነዚህን ኢትዮጵያውያን እነዚህን ባንዳዎች እንደ ቀደመው ሁሉ በሚገባቸው ቋንቋ እያናገሯቸው ይገኛል፡፡

የዘመናችን ባንዳዎች በራሳቸው እርካብ የሚፈናጠጡ፤ በራሳቸው ልጓም የሚታዘዙ አይደሉም፡፡ ይልቁንም የመወጣጫ እርካብ፤ የመመሪያ ልጓማቸውን በልክ ሰፍተው የሚያሰሟሯቸው ከማዶ ሆነው በገንዘብም በቴክኖሎጂም በሃሰት ፕሮፖጋንዳም የሚያግዟቸው አሜሪካ እና ግብረአበሮቿ እንጂ፡፡ ለዚህም ነው ትናንት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያለውን ውጥንና የአገር መከላከያ ሰራዊትን በማጥቃት የተገለጠውን አሸባሪውን ሕወሓት ኢትዮጵያ አሸባሪ ብላ ስትፈርጅ፤ የአሸባሪዎች መድሃኒት ነን ብለው የሚደነፉት እነዚህ አገራት ከኢትዮጵያ በተቃራኒው መቆማቸው፡፡

ትናንት አሸባሪ ቡድኑ የባንዳነት ተልዕኮውን ይዞ በትግራይ የፈጸመው አልበቃ ብሎት በአማራና አፋር ክልሎች ወረራን ፈጽሞ ንጹሃንን በጅምላ ሲጨፈጭፍ፤ ሃብትና ንብረት ሲዘርፍና ሲያወድም እንዳላየ ያለፉትም ለዚሁ የተልዕኳቸው ፈጻሚነቱ ከዳር እንዲደርስላቸው በመመኘት ነበር፡፡ ይህ ህልማቸው ግን ዳግም በኢትዮጵያውያን ክንድ ቅዠት ስለሆነባቸው፤ ሁለተኛውን መጠባበቂያ ለመጠቀም በመፈለግ ፊታቸውን ወደ አሸባሪው ሸኔ አዙረዋል፡ እናም ለአሸባሪው ሕወሓት የጫና መቀነሻ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ዘመቻውን በአንድ እጃቸው፤ በሌላኛው ደግሞ አሸባሪውን ሸኔ ለማጀገን የሚያስችሏቸውን ተመሳሳይ ስልት መተግበር ስራቸው ሆኗል፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን ይህ ሁሉ ሴራ፣ ጫናና የውስጥ ባንዳዎች የተቀናጀ ዘመቻ እጃቸውን የሚጠመዝዛቸው አልሆነም፡፡ ይልቁንም ይህ የባዕዳንና ባንዳዎች ጫናና የተቀናጀ ዘመቻ ለመሰባሰብና መተባበራቸው አንቂ ደወል ሆኖላቸው በአንድ ግንባር ተሰልፈው በጠቅላይ ሚኒስትራቸው ፊት አውራሪነት የውስጥም የውጪም ጠላቶቻቸውን መደምሰስ ይዘዋል፡፡ በዚህም ትናንት በዓድዋ የተዋረዱ ኃይሎች ዳግም ለውርደት ሲንደረደሩ፤ ተላላኪ ባንዳዎቻቸው ደግሞ ወደ ሞት ሲገሰግሱ እየታየ ነው፡፡

ይህ ደግሞ የኢትዮጵያውያን ከጥንት የመጣ የታሪክ ገጽታና ያልተቆራረጠ ገድል ሲሆን፤ ጀግኖችን ማሞገስና ማጀገን ብቻ ሳይሆን ባንዳዎችን ለሌሎች ማስተማሪያ በሚሆን መልኩ መቅጣት የተካኑበት መሆኑን ማሳያም ነው፡፡ ትናንት በዓድዋ አሁን ደግሞ በዳግም ወረራቸው ወቅት በባንዳዎች እየታገዙ ሞክረው ያቃታቸውን ኢትዮጵያን የማንበርከክ ህልም፤ ዛሬም በተላላኪዎቹና ባንዳዎቹ አሸባሪዎች ሕወሓትና ሸኔ አማካኝነት እውን ለማድረግ የነበራቸውን ምኞት የኢትዮጵያውያን ክንድ እንደጉም አትንኖባቸዋል፡፡ ይህ የታሪክ ጉዞም ኢትዮጵያን ከውጭ ሆነው ለማንበርከክ የሚመኟት ኃይሎችም ሆኑ በኢትዮጵያ ምድር የሚበቅሉ ባንዳዎች እጣ ፈንታቸው ውርደት እና ሽንፈት መሆኑን በአደባባይ ያረጋገጠ ነው፡፡

አዲስ ዘመን ኅዳር 25/2014

Recommended For You