ችግሮች የፈተኑት የኮቪድ-19 ክትባት

የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚያዚያ ወር 2013 ዓ.ም 20 ከመቶ ያህሉን ህዝቧን ሊከትብ የሚችል የአስትራዜኒካ ክትባት ‹‹ኮቫክስ›› ከተሰኘው ዓለም አቀፍ የክትባት ጥምረት ተረክባ ወደ ሀገር ውስጥ አስገብታለች:: በወቅቱም ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ ማለትም የጤና ባለሙያዎች፣ እድሜያቸው የገፉና ተደራራቢ የጤና ችግር ያለባቸውና ተጨማሪ የሥራ ኃላፊነት ያለባቸው የጥበቃ ኃይሎች ክትባቱን እንዲያገኙ ተደርጓል::

በሂደት ደግሞ ተጨማሪ ሲኖፋርምና ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የተሰኙ ክትባቶችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት በየደረጃው ያሉና ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ክትባቱን እንዲያገኙ ተደርጓል:: ክትባቱን በማሰራጨት ሂደት ታዲያ ከህብረተሰቡ በኩል በተለያዩ ምክንያቶች ክትባቱን ላለመከተብ ማንገራገሮች ታይተዋል::

ወትሮውንም ለአፍሪካ ሀገራት የክትባት ስርጭት ኮታ አናሳ መሆን ከክትባቱ ዋጋ ጋር ተዳምሮ ከኢትዮጵያ የህዝብ ቁጥር አንፃር ክትባቱን ለዜጎች ለማዳረስ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም በህብረተሰቡ በኩል በተሳሳተ ግንዛቤ ምክንያት ክትባቱን ለመውሰድ አለመፈለግ ትልቅ ችግር ሆኖ ቆይቷል:: በጊዜው ከነበረው ዓለም አቀፍ የክትባት ሽሚያ ጋር በተገናኘም በኢትዮጵያ አቅም ክትባቱን ማግኘት አስቸጋሪ ነበር::

በሂደት ግን ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው የክትባት መጠን እያደገ መምጣቱን ተከትሎ የጤና ሚኒስቴር በመጀመሪያ እድሜያቸው አስራ ስምንትና ከዛ በላይ የሆኑ ዜጎች በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የመንግሥት ጤና ተቋም ሄደው ክትባቱን እንዲወስዱ ውሳኔ አሳልፏል:: በቅርቡ ደግሞ በስልሳ ሁለት የሀገሪቱ ከተሞች አሥራ ሁለት ዓመትና ከዛ በላይ የሆኑ ልጆች የኮቪድ-19 ክትባት በዘመቻ እንደሚሰጣቸው አስታውቋል::

በጤና ሚኒስቴር የብሄራዊ ክትባት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዮሐንስ ላቀው እንደሚሉት እስከአሁን ባለው ሂደት 14 ሚሊዮን ዶዝ የሚጠጋ የኮቪድ-19 ክትባት ገብቷል:: ከእነዚህ ውስጥ አራት ዓይነት ክትባቶች ለህብረተሰቡ እየተሰጡ ይገኛሉ:: እነዚህም አስትራዜኒካ፣ ሲኖፋርም፣ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ፋይዘር የተሰኙት ሲሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተሰጡ ያሉና የኮቪድ-19 በሽታን ለመከላከል የሚያገለግሉ ብሎም በሽታው የሚያደርሰውን ስቃይና ሞት ከመቀነስ አንፃር ጉልህ ሚና የሚጫወቱ ናቸው::

እንደ አስተባባሪው ገለፃ እስካሁን ከገባው 14 ሚሊዮን ዶዝ ክትባቶች ውስጥ በዘመቻ መልክ የሚሰጠውን ክትባት ጨምሮ ከ9 ሚሊዮን ዶዝ በላይ ተሰጥቷል::

 አሁንም ክትባቱ በዘመቻ መልክ ቀጥሏል:: የኮቪድ-19 ክትባቶች ገና መተዋወቅ ሲጀምሩ በመጀመሪያ ጤና ሚኒስቴር ያቀደው 20 ከመቶ ያህሉን የህብረተሰብ ክፍል ለመከተብ ነበር:: ይህም ሊሆን የቻለው በጊዜው ዓለም አቀፍ የክትባት ሽሚያዎች በመኖራቸውና ይህንኑ ተከትሎ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ታዳጊ ሀገራት ክትባቱን ለማግኘት በመቸገራቸው ነው:: ክትባት አምራች ሀገራትም ቅድሚያ ለራሳቸው የመስጠት አዝማሚያም ይታይ ነበር:: ከዚህ ጋር ተያይዞም ክትባቱን ባለው ጊዜና ፍጥነት የማግኘት ዕድል አልነበረም::

ይሁንና በአሁኑ ጊዜ ክትባቶቹን በብዛትና በዓይነትም ጭምር የማግኘት ዕድል ተፈጥሯል:: ከዚህ አንፃር የጤና ሚኒስቴር እቅድ እስከ ታህሳስ 30/ 2013 ድረስ 20 ከመቶ የሚሆነውን ህብረተሰብ ክፍል ለመከተብ የነበረ ቢሆንም ቀደም ሲል የነበሩ ችግሮች እንዳሉ ሆነው እስካሁን ባለው ሂደት 10 ከመቶ ያህሉ የህብረተሰብ ክፍል ተከትቧል:: አሁንም ክትባቱ እየተሰጠ በመሆኑ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ በሀገር አቀፍ ደረጃ 20 ከመቶ ያህሉ የህብረተሰብ ክፍል ክትባቱን ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል::

ዓለም አቀፍ የክትባት አቅርቦትና ሌሎችም ሁኔታዎች ከተሻሻለ ደግሞ ከተቀመጠው አቅድ በላይ ለመሄድ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ:: ከዚህ ባለፈ የህብረተሰቡ ክትባቱን ለመከተብ አለመፈለግም እቅዱ በተፈለገው ልክ እንዳይሳካ የራሱን አስተዋፅኦ አድርጓል:: ይሁንና የጤና ሚኒስቴር እነዚህን ውጣውረዶች ሁሉ አልፎ ክትባቱን ለህብረተሰቡ ለመስጠት ጥረት እያደረገ ይገኛል:: ሀገሪቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ሆና ክትባቱን ለዜጎች ለማዳረስ ጥረት እየተደረገም ነው::

አስተባባሪው እንደሚያብራሩት መጀመሪያ አካባቢ ክትባቱ ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ አተኩሮ ሲሰጥ ነበር:: በዚህም እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች በክትባት ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ ጥረት ተደርጓል፤አብዛኛዎቹም ክትባቱን አግኝተዋል:: ይሁንና በየትኛውም የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ክትባቱን ይፈልጋሉ:: እድሜያቸው ከአሥራ ሁለት ዓመት በላይ የሆኑና ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ ህፃናት ሊኖሩም ይችላሉ::

መጀመሪያ አካባቢ የነበሩት ክትባቶች እንዲሰጡ በጥናት የተረጋገጠው እድሜያቸው አሥራ ሰባትና ከዛ በላይ ለሆኑ ሰዎች ነው:: ይሁንና በቅርቡ ፋይዘር የተሰኘው የክትባት አይነት በህፃናት ላይ ሙከራ ተደርጎ ውጤታማነቱ ከተረጋገጠ በኋላ ፍቃድ አግኝቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ እድሜያቸው አስራ ሁለት ለሞላቸው ህፃናት እየተሰጠ ይገኛል::

በተመሳሳይ በኢትዮጵያም በትምህርት ቤቶችና በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚገኙ ህፃናት ክትባቱን ማግኘት እንዳለባቸው ከግምት ውስጥ በማስገባትና የበሽታውን ስርጭት ለማቆም በሀገር አቀፍ ደረጃ በ62 ከተሞች የሚገኙና እድሜያቸው አሥራ ሁለትና ከዛ በላይ የሆናቸው ልጆች የፋይዘር ክትባት በዘመቻ መልክ እንዲሰጣቸው ውሳኔ ተላልፏል:: ይህ ሲባል ግን አሁንም ለበሽታው ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ፣ እድሜያቸው ለገፋና ተጓዳኝ ህመም ላለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ቅድሚያ ይሰጣል::

ይሁንና ዋነኛው አላማ የበሽታውን ሥርጭት ለማቆም በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እየተከተበ መሄድ አለበት የሚል አቅጣጫ ከጤና ሚኒስቴር ወርዷል:: በሽታውን በማሰራጨት ረገድ በኩል ሁሉም ተዋናይ በመሆኑ ክትባቱ ከአሥራ ሁለት ዓመት እድሜ ካሉት ጀምሮ እንዲሰጥ ተወስኗል:: ይህም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በክትባት ተደራሽ እየሆነ በሄደ ቁጥር የበሽታውን ከሰው ወደ ሰው ስርጭት ለማቆም ያግዛል::

ከተለያዩ የተሳሳቱ መረጃዎች ጋር በተገናኘ ሰዎች ክትባቱን አስመልክቶ በውስጣቸው ጥርጣሬ እንዲኖር አድርጓቸዋል:: ነገር ግን በርካታ ሰዎች እየተከተቡ ሲሄዱ የህብረተሰቡን በራስ መተማመን ማሳደግ ይቻላል:: ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ጤና ሚኒስቴር ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል::

አስተባባሪው እንደሚገልፁት ክትባቱን እየወሰዱ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉ ሁሉ ክትባቱን ላለመውሰድ የተለያዩ ምክንያቶችን የሚያቀርቡም አሉ:: እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ክትባቱን ገሚሶቹ ከፖለቲካና ሃይማኖት ጋር ሌሎቹ ደግሞ ከክትባቱ የጎንዮሽ ጉዳት ጋር ለማገናኘት ይሞክራሉ:: ከዚህ አኳያ ስለክትባቱ በቂ መረጃ በመስጠትና በማሳመን ህብረተሰቡ እንዲከተብ ማድረግ ይገባል::

ከዚህ አንፃር እንደ ጤና ሚኒስቴር ክትባቱን አስመልክቶ በተለያዩ አጋጣሚዎች ልዩ ልዩ ሚዲያዎችን በመጠቀም፣ የሃይማኖት አባቶችን በማሳተፍና የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላትን በማወያየት ግንዛቤ ለመስጠት ጥረት ተደርጓል:: በየጎዳናው በመቀስቀስና ተፅእኖ ፈጣሪ የሚባሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን በመጠቀም ከክትባቱ ጋር በተያያዘ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሻሻል ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ:: በዚህም ለውጥ ማምጣት ተችሏል:: ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ እስከ 4 ሚሊዮን የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ክትባቱን ወስደዋል:: ነገር ግን አሁንም ገና ያልተከተቡ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች በመኖራቸው ይህ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል::

ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡት አብዛኛዎቹ ክትባት የአገልግሎት ዘመን በጣም አጭር ከመሆኑ አኳያም ቅስቀሳዎች ተደርገው ለመከተብ ፍቃደኛ ያልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ያሉባቸው አካባቢዎች ላይ የክትባቶቹ የአገልግሎት ጊዜ ሊያልፍ ይችላል:: ነገር ግን ይህ እንዳይከሰት ክትባቶቹን ከቦታ ቦታ በመቀያየር ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲከተቡ ይደረጋል:: ክትባት ለመውሰድ ፍቃደኛ ያልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ባሉባቸው አካባቢዎች ደግሞ ተጨማሪ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን በመስጠት ክትባቱን እንዲወስዱ ሥራዎች ይሰራሉ::

በተለያዩ ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ምክንያቶች የክትባቱ ሂደት በርካታ ፈተናዎች አጋጥመውታል:: ይሁንና በአሁኑ ጊዜ የክትባት አቅርቦቱ እየጨመረ በመሄዱና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው የክትባት መጠንም ከፍ በማለቱ ህብረተሰቡ ራሱንና ሌሎችን ከኮቪድ-19 ለመጠበቅ ነገ ዛሬ ሳይል ክትባቱን እንዲወስድ ይመከራል:: ከተሳሳቱ መረጃዎች ጋር በተገናኘም ህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ ካላቸው አካላት መውሰድ ይጠበቅበታል::

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ኅዳር 25/2014

Recommended For You