ለመጀመር መጀመር!

በዙሪያችን ያለው ሁሉ የመጀመር ውጤት ነው። ይህን ጽሁፍ የምጽፍበት ኮምፒውተር በጅምር ሂደት ውስጥ አልፎ ዛሬ ላይ የደረሰበት ደረጃ ላይ የደረሰ ነው። የእጅ ስልካችን ከስልክነት አልፎ ብዙ ነገር ከመሆኑ በፊት እንዲሁ በመጀመር ምዕራፍ ውስጥ አልፏል። በተንቀሳቃሽ ስልካችን ዙሪያ በመጀመር ምዕራፍ ውስጥ ያለፉትን ስናነሳ ብዙዎችን እንጠቅሳለን። ለአብነት ያህል የእጅ ስልካችን ውስጥ ያሉ አስገራሚ መተግበሪያዎች/applications ላዘጋጇቸው ሰዎች የመጀመርና ያሰቡበት ጋር የመድረስ ማሳያዎች ናቸው።

ቤታችን ቁጭ ብለን ዓለምን በቴሌቪዥን መስኮት እንድንቃኝ ያደረገን ቴክኖሎጂም እንዲሁ የመጀመርና የጀመሩትን ዳር የማድረስ ሂደት ውጤት ነው። ፍጥረት በሚለው ስም የሚጠሩት ሁሉ በፈጣሪ የመፍጠር ጅማሮ ውስጥ ትርጉም የተሰጣቸው ሆነው በመገኘታቸው ውስጥም የመጀመር ትርጉም አለ። በግል ህይወታችን ውስጥስ? የዛሬ ገጻችን ስለ መጀመር የሚዳስስ ነው። ለመጀመር መጀመር! አቶ አስባለሁን አንስተን ወደ ሁለት ወጣቶች የፓርኪንግ አገልግሎት መስጫ እንዘልቃለን።

አቶ አስባለሁ

ብዙ ጊዜ የጀመርነውን ዳር ስለማድረስ ወይንም ስለመጨረስ ስናስብ እንገኛለን። ልክነው የጀመርነውን ለመጨረስ ማሰብ አለብን። ዛሬ ግን ስለጀመርነው ሳይሆን ስላልጀመርነው ነገርግን ለመጀመር ስለምናስበው ነው። መጀመር የቻሉ በትጋትና በትእግስት መሰላል አልፈው ወደ መዳረሻ ለመድረስ እንደሚራመዱ እንዲሁ ያልጀመሩ ለመጀመር በሚያደርጉት ጉዞ ውስጥ የሚያስፈልጋቸውን ስንቅ ሊሰንቁ ይገባልና።

ለእኛ ኢትዮጵያውያን መጀመርም ሆነ የተጀመረውን ወደ ዳር ማድረስ ከባድ በሆነበት ድባብ ውስጥ ማለፍን እንደሚጠይቅ ብዙ አስረጂ የሚያስፈልገን አይመስልም። በዙሪያችን ያለው በሙሉ ችግርን የሚናገር ያሰቡትን ለማሳካት ከባድ መሆኑን በውብ ቃላት የሚያስረዳ ሆኖ ስለሚታይ። በተቃራኒው ግን የአስባለሁ ንግግርም በሰፊው አለ። በስሜት ውስጥ ተሁኖ “እኔ እኮ እንዲህ ማድረግ አስባለሁ።” ሲባል ይሰማል። “ይህና ይህ ቢሆንልኝ እንዲህ ማድረግ አስብ ነበር።” ይላል ሌላው።“እንትናን ባገኘው እኮ ይህን ለማድረግ አስባለሁ።” ተረኛው ይቀጥላል። “ይህን ያህል ገንዘብ ቢኖረኝ እኮ ይህን ማድረግ አስባለሁ።” የሌላው አቶ አስባለሁ ድምጽ። ብዙ አስባለሁ፤ ብዙ አቶ አስባለሁ።

ሰዎች ስሜትን በሚያነቃቃ ድባብ ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ ያልተጀመረው ተጨርሶ ይታየንና በአቶ አስባለሁ መንፈስ ከፍታው ላይ በቀላሉ አልጋ በአልጋ በሆነ መንገድ ደርሰን ራሳችንን እናገኘዋለን። ነገር ግን የአቶ አስባለሁ የስሜት ድባብ ሲቀዘቅዝ ካለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ስንገናኝ ግን መጀመር ቀላል አለመሆኑን አስበን ባለንበት ተጨማሪ ቀን እንረግጣለን። እዚያው መርገጥ፤ በቢሆን እሳቤ አሻግሮ እያዩ መልሶ እዚያው መርገጥ።

ሁለቱ ወጣቶች የፓርኪንግ ስራ የሚሰሩበት አካባቢ ካለው የጀበና ቡና ቤት ውስጥ ቡናቸውን እየጠጡ ናቸው። ወደ ፓርኪንግ ስራ የገቡት አስበውበት ሳይሆን በድንገት ነው። ሰፈራቸው የሚቆም መኪናን እየጠበቁ የሚሰጣቸውን ሳንቲም መልቀም ጀምረው በእዚያው ቀሩ። ስራውን የወደዱት ምንም ሳይለፉ ገንዘብ በመልቀማቸው እንደሆነ ይሰማቸዋል። ቆሞ ከተነሳ መኪና ሁሉ ሄዶ ገንዘብ እየተቀበሉ የእለት ፍላጎትን እያሟሉ መንገድ ዳር መዋል።

አንድ ቀን እንደለመዱት የፓርኪንግ ሊቀበሉ ወደሚንቀሳቀስ መኪና ሄዱ። ተረኛው ወጣት ወደ ሹፌሩ አቅጣጫ ሲጠጋ የገጠመው ገንዘብ ሳይሆን የተኮሳተረ ፊት ነበር። ባለመኪናው “አቤት” አለ፤ ወጣቱም “የፓርኪንግ አለ። ባለመኪናው “ፓርኪንግ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ። ወጣቶቹም እርስበርሳቸው ተያዩና “መኪናህን ያቆምክበት ነዋ!” ሲሉ መለሱ። ግለሰቡም “መኪናዬን ያቆምኩበት ቦታ ላይ የፓርኪንግ አገልግሎት አላገኘሁም። የፓርኪንግ አገልግሎት ማለት መኪና ሲገባ መንገድ አሳይቶ፤ ሲወጣ ደግሞ በመውጣት ረድቶ፤

 መኪናው እየተጠበቀ መሆኑን የሚያሳይ ትምምን ፈጥሮ ሲደረግ የሚሰጥ አገልግሎ ነው። ልክ መኪና ሲወጣ ፓርኪንግ ስራ እየሰራችሁ መሆኑን የሚያሳይ ዩኒፎርም ለብሳችሁ መጥታችሁ ብር መጠበቅ እርሱ ፓርኪንግ አይደለም። እኔ ስገባ አንዳችሁም መጥታችሁ አገልግሎት አልሰጣችሁኝም። ወጥቼም ስሄድ እየተጠበቀልኝ መሆኑን አላውቅም እንዲሁም ስወጣ አልረዳችሁኝም፤ እና ምን አገልግሎት አገኘሁ ብዬ ልክፈል? አላቸው።” ሁለቱ ወጣቶች እርስበርሳቸው ተያዩ። የሰውዬው ሃሳብ አሳማኝነት ያለው ቢሆንም ከእዚህ ቀደም የሚያደርጉትን ተመሳሳይ ነገር አድርገው ገንዘብ በማጣታቸው ግን ተበሳጩ። ከሁለቱ ወጣቶች አንዱ ግን የባለመኪናው ሃሳብ በጣም ስላሳመነው ዝምታን መረጠ። ጎደኛው ግን ሌላ ጊዜ ይስተካከላል ለአሁኑ ገንዘባችንን ስጠን ብሎ ቡራከረዩ አለ። ባለመኪናውም ወይ ፍንክች ብሎ ሳይከፍል ሄደ።

ሁለቱም ወጣቶች ወደሚቀመጡበት ቦታ ተመለሱ። የሹፌሩ ሁኔታ ያሳመነው ወጣት ከሹፌሩ ወደ ውስጡ የገባ እይታን አግኝቷል። መወያየት ጀመሩ። ባለመኪናው ያለው እውነቱን እንደሆነ የፓርኪንግ አገልግሎትን በአግባቡ ለመያዝ ሥራዬ ብለው መስራት እንዳለባቸው አሰቡ። ከውይይታቸውም በኋላ ስለ ፓርኪንግ አገልግሎት አንብበው በተደራጀ መንገድ አገልግሎቱን ለመስጠት፤ የመኪና እጥበትም ለመጨመር፤ እንዲሁም ለመኪናዎች የሚሆን ቁሳቁስ ሽያጭም እንዲኖራቸው ስለማድረግ ወዘተ መከሩ። እየመላለሱ ብዙ መከሩበት።

ባሰቡት መንገድ ለመጀመር ግን እንደ መጀመሪያው መኪና ቆሞ ሲንቀሳቀስ ገንዘብ እንደመጠየቅ ቀላል አልሆነም። ቦታ ማመቻቸት፣ ብድር መፈለግ፣ የእቃ ግዢ ማከናወን፣ ደረሰኝ ማሳተም፣ ወዘተ ተራራ መውጣት ሆነባቸው። አንደኛው ወጣት ባለው ቁርጠኝነተ ያሰቡትን ማድረግም ቻሉ። ሌላኛውም ጎደኛው የሚሆነውን ለውጥ እያየ በጀመሩት አዲስ ስራ ተደስቶ አብረው ዘለቁ። ስለ መጀመር …

ሁለቱን የምናብ ወጣቶች ስለ መጀመር እያደረጉት ያለውን ዝግጅት ለእነርሱ ትተን ወደ ጉዳያችን ስንመለስ መጀመር ሲታሰብ የሚሟገቱትን ሁለት የእኛ አካሎችን እናንሳ። ልባችንና አዕምሮችን።

መጀመር ሲታሰብ … የልብ እና የአዕምሮ ሙግት

ማርቲን ሉተር ኪንግ የመጀመሪያውን እርምጃ በእምነት ተራመድ ይላል። የመጀመሪያውን እርምጃ በእምነት ለመራመድ ግን ውስጣዊ ስምምነት ያስፈልጋል። ልባችን በእምነት ለመራመድ ሲነሳ አእምሯችን ደግሞ እርምጃውን በስሌት ስለማድረግ ይሞግተናል። ስለሆነም መጀመር ሲታሰብ ውሳኔ ለመወሰን ሁለት ፌርማታዎች ላይ ጊዜ እንወስዳለን፤ በልባችን እና በአእምሮችን።

አእምሮችን ምክንያታዊ ለመሆን ይፈልጋል። ባለን የገንዘብ መጠን፣ ባለን ቁሳቁስ፣ ባለን ጊዜ ወዘተ ውስጥ መጀመርን ግምት ውስጥ አስገብቶ ትርጉም ለመስጠት ይፈልጋል። አዲስ ነገር ለመጀመር እንዲሁም ዛሬ በእጃችን ያለውን ወደፊት ለመግፋት በምክንያታዊነት እያሰቡ መራመድ አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይደለም። ምክንያታዊነት ለማንም ሰው የሚያስፈልግ መሆኑን መቼም ልንክድ አንችልም። ብር የሚሰራው ብዙ ስራ መኖሩም እንዲሁ ግልጽ ነው። የቁሳቁስ ግብዓትም አይዘነጋም። ሁለተኛው ፌርማታ ውስጥ ግን የበለጠው ጉልበት፤ የበለጠው የመጀመር አቅም፤ የበለጠው ወረት አለ፤ እርሱም በልባችን ውስጥ የሚሆነው የመጀመር የእምነት ውሳኔ።

በልባችን ውስጥ ወኔ አለ፣ በልባችን ውስጥ ለመሰጠት የምንሄድበት እርቀት አለ። ገንዘብ ያለው፤ ነገርግን ልብ የሌለው ወደ ውጤት ሊደርስ እንደማይችል ዞር ዞር ብንል አንዳች ምስክር አናጣም። ከልብ አደርጋለሁ ብሎ መነሳት ለመጀመር መጀመሪያው ነው። የእችላለሁ መንፈስ ከአእምሮ ምክንያታዊነት ባለፈ ከውስጥ በሚወጣ እምነት ውስጥ ይወለዳል።

በተቻለው መጠን ግን የአዕምሮን ጥያቄም ለመመለስ መቻል ተገቢነቱ አያጠያይቅም። ሰዎች የሚጀምሩት ነገር ያለውን ሪስክ/risk ተመልክተው ውሳኔያቸውን እንደራሳቸው ሁኔታ ያሳልፋሉ። አንዳንድ ሰዎች ሪስክ/risk በቀላሉ ሲቀበሉ፤ ሌሎች ደግሞ ለመመጠን ሲሞክሩ እንዲሁም አንዳንዶች ደግሞ ፈጽሞውኑ ሪስክ/risk

 ሲያስወግዱ ነገርግን ባላቸው ነገር ላይ ሙጥኝ ብሎ መቀመጥን ሲመርጡ ይታያሉ። በተለይ እድሜያችን እየጨመረ ሲመጣ አዳዲስ ነገር ከመጀመር ይልቅ በእጃችን ያለውን አጠንክረው መያዝ ላይ እናተኩራለን። ይህ የሚሆንበት ምክንያት በአእምሮ በሚደረግ ውሳኔ ለአዳዲስ ነገር ሪስክ ላለመውሰድ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል። በወጣትነት እድሜ ደግሞ አዳዲስ ነገርን ለመጀመር በትጋት መነሳሳት ይታያል።

የተጀመረ ሁሉ ወደ ፍሬ እንዲመጣ ለመጀመር መወሰን ቀዳሚው ነገር ነው። ለመጀመር ደግሞ የሚወሰድ ሪስክ/risk ሊኖር ይችላል። ምክንያቱም ሁሉም ነገር ተመቻችቶ ለመጀመር የሚቻልበት አንድም ቀን ስለሌለ። ምንም ሳይኖር የሚጀመርም ነገርም ስለሌለ። ዛሬ በውስጣችን ያለ ወደ ፍሬ ልንቀይረው የሚገባን ነገር ወደ ፍሬ ለመቀየር ለመጀመር ዝግጁ መሆን አለብን፤ ከውስጣችን ድምጽ ከልባችን መልዕክት ተነስተን። ተገቢውን አዕምሯዊ ስሌትም በማድረግ።

አዲስ የምንጀምረው ነገር ካለ ሁሌም ልንጠይቀው የሚገባው ጥያቄ ‘ዛሬ ካልሆነ መቼ?’ የሚለውን መሆን አለበት።

ዛሬ ካልሆነ መቼ?

“አዲስ ጅማሮ የሌላ ጅማሮ ፍጻሜ ነው” የሚባል አባባል አለ። መቆም ያለበትን ነገር ለማቆም፤ መጀመር ያለብንን ነገር ለመጀመር ዛሬ ከሁሉ የተሻለው ቀን ነው። ‘ዛሬ ካልሆነ መቼ?’የሚለው ጥያቄ እያንዳንዱ ለመጀመር የሚያስብ ሁሉ ሊጠይቀው የሚገባ ጥያቄ ነው። ከዛሬ ይልቅ ነገ በክፋትም በውስብስብነት ይጨምር ይሆናል ብሎ በማሰብ ለዛሬ ቦታ መስጠት አስፈላጊ ነው። የብልህ ሰው መገለጫነቱ ለዛሬ የሚሰጠው ትርጉም ነውና።

ዛሬን መጠቀም ማለት ዛሬ ላይ መወሰን ያለበትን ነገር በመወሰን ይገለጻል። በዛሬ ከሚደረጉ ውሳኔዎች መካከል መጀመር የሚገባንን መጀመር ዋናው ነው። ለመጀመር የዛሬን ትርጉም በአግባቡ መረዳትም ያስፈልጋል።

ለዛሬ የሚገባውን ትርጉም ሰጥቶ ለመጀመር የሚራመድ ሰው ግምት ውስጥ ሊያስገባቸው የሚገቡ ቁልፍ አምስት ነጥቦችን እንመልከት። አዲስ ነገር ለመጀመር ስናስብ በመነቃቃት ውስጥ መጀመር እንድንችል የሚያደርጉንን ቁልፍ አምስት ነጥቦች አሉ።

1. ‘ለምን?’ ለሚለው ጥያቄ ግልጽ መልስ ማግኘት – ማንኛውም አዲስ የምንጀምረው ነገር ውስጥ ልናሳካ የምንፈልገው ነገር ላይ የሚኖረን ግልጸኝነት ስራውን ለመጀመርም ሆነ በአግባቡ እያሳደጉ ለመሄድ እድልን ይሰጣል። በመሆኑም ‘ለምን?’ የሚል ጥያቄን እየመለስን ለመሄድ መስራት አለብን። በመነሻችን ላይ ያነሳናቸው ወጣቶች ‘እንዲሁ ብር ከመቀበል ለምንድንነው ገንዘብ መቀበል ያለብን?’ የሚለውን ጥያቄ መመለስ ሲጀምሩ ሌሎች ተጓዳኝ ስራዎችን ማየት እንዲችል እድል እንደሆናቸው መረዳት አለብን።

2. ውድቀትን የምናይበትን መንገድ መስተካከል – ሔነሪ ፎርድ “ውድቀት እንደ አዲስ በጥንካሬ ለመነሳት የቀረበ እድል ነው” ይላሉ። አባባሉ ውደቀት አልመን የምንሄድበት ባይሆንም ሲመጣ ግን ለወደፊቱ የሚሆን አቅም የሚገኝበት መሆኑን የሚያመላክት ነው። ማንም ሰው ቢሆን ውደቀትን አይፈልገም። እንዴት ሰው መውደቀን አስቦ ስራ ሊሰራ ይችላል? በፍጹም! ነገርግን ነገሮች እኛ እንዳሰብነው ሊሄዱም ሆነ ላይሄዱ ይችላሉ። ስለሆነም ደረጃው ይለያይ እንጂ በጉዟችን ውስጥ መውደቅ የሚባል ነገር አለ። መውደቅ ግን ወድቆ መቅሪያ እንዳይሆን ወደ ትምህርት እድልነት በመቀየር ልንጠቀምበት ይገባል። ዛሬ በወደቅንበት ነገር ነገም በተመሳሳይ ሁኔታ ልንወድቅበት እንዳንችል ትምህርት ወስደን የምናልፍበት መሆን አለበት።

3. ትንንሽ ስኬቶችን ማክበር – መጀመር ላይ ለመድረስ ትንንሽ ስኬቶችን በማክበር የመቻልን ስነልቦና ማዳበር አለብን። ትልቅ ስኬት የሚመጣው እያንዳንዱ ትንንሽ ስኬት ሲደመር መሆኑን በመረዳት። በመሆኑም ትንንሽ ስኬቶችን እየደመርን ልናከብራቸው ይገባል። ራሳችን ላይ የማይሆን ቃል ከመዝራት፤ የጎደለው ነገር ብቻ የሚታየን ከመሆን ወጥተን ስኬትን አክባሪ መሆን አለብን፤ ትንሽም ቢሆን። በጉዟችን ውስጥ ያሉትን ጥቃቅን የሚመስሉ ድሎችን ቆጥረን ፈጣሪን ልናመሰግን እንዲሁም ለስኬቱ መገኘት ምክንያት የሆኑ አካላትን

 ልናደንቅ ይገባናል።

4. እያንዳንዱን ቀን አክብሮ መጠቀም – የአጸደህጻናት ትምህርት ቤት የመጀመሪያው ቀን በተማሪነት ህይወት ውስጥ ልዩ ትርጉም አለው። ትምህርት የሚባለው ህይወት የሚጀመርበት የመጀመሪያው ቀን። አዲስ ነገር ስንጀምርም እያንዳንዱን ቀን ልክ እንደ አዲስ መጀመሪያ ቀን ቆጥረን በበቂ ዝግጅትና በተነቃቃ ድባብ ልናስኬደው ይገባል። እኛ ውስጥ የተፋዘዘ ቀን በስራዎቻችን ላይም የተፋዘዘ ቢሆን ሊገርመን አይገባም። በመሆኑም እያንዳንዱን ቀን እንደ ልዩ ስጦታ ቆጥረን በትጋት ልንሰራበት ወደ ፍሬም ለመድረስ እንደ መሰላሉ አንዱ መወጣጫ ልናየው ይገባል። መጀመርና የጀመሩትን ዳር ማድረስ ውስጥ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ለቀኖቻችን የተገባውን ስፍራ ልንሰጥ ይገባናል። አዲስ ነገር ስንጀምር ደግሞ ይበልጥኑ።

እያንዳንዱን ቀን አክብሮ በመመልከት ውስጥ ለመነቃቃት የምንሰጠው ቦታም አለ። አዲስ ነገር ለመጀመር መነቃቃት አስፈላጊ ግብዓት ነው። የመነቃቃት ምንጩ የምንወስደው አነቃቂ መጠጥ ሳይሆን የምንሰራው ስራና የምናልመው ውጤት ውስጥ መሆን አለበት። እያንዳንዱ ቀን በምንሰራው ስራ ውስጥ በመነቃቃት ስንመለከተው ቀኑን በፍሬ እንጠቀምበታለን። ብዙ ሰዎች ቢያንስ አንድ አዲስ ነገርን በህይወታቸው ለመጀመር ወይንም አንድ ነገርን ለመቀየር ያስባሉ። ለመጀመር የሚያስፈልገውን መነቃቃት ግን ያጡታል። መነቃቃት ምን እንደሆነ መረዳት ለእዚህ ወሳኝነት አለው።

መነቃቃት ግብ ያደረግነውን ነገር ወይንም ፍላጎታችንን ለማሳካት የሚነዳን ወይንም የሚያነሳሳን ነው። ግብህን የምትወድበት መጠን እና ብታሳካው ልታገኘው እንደምትችል የምታስበው መነቃቃትን የመፍጠር አቅም አለው። መነቃቃት አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ልታሳካው ከምትፈልገው ግብ አንጻር የተቃኘ እንቅስቃሴን እንድታደርግ ስለሚረዳ፣ ችግሮችን ለመፍታት ስለሚያግዝ፣ የትላንት አላስፈላጊ የሆኑ ልማዶችን ለመቀየር ስለሚያግዝ፣ ተግዳሮትንና እድልን ለመጋፈጥ ስለሚያስችል ነው።

5. ስኬትን መመልከት – በልብና በአዕምሮ ሙግት ውስጥ ወደ ልባችን የምናደላው ልባችን ከሁኔታዎች ሁሉ በላይ ስኬት ላይ ለመድረስ ሁነኛ በመሆኑ ነው። ስኬትን በልባችን አሻግረን መመልከት አለብን። በምንጀምረው ስራ ውስጥ ምን ይታየናል? ስኬት ወይንስ አለመከናወን? መልካም ጅማሮን ለማድረግ የሚነሳ ሰው በፍጹም አለመከናወን ሊታየው አይገባም። ልናሳካው እንደምንችል ብቻ ማየት ይኖርብናል። ስኬትን መመልከት ወደ ስኬት የሚያመራውን መንገድ እንድናገኝ ያደርገናል። በመሆኑም እይታችን ሁልጊዜ ማሸነፍ፤ ያሰቡበት ጋር መድረስ መሆን መቻል አለበት።

በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ

አዲስ ዘመን ኅዳር 25/2014

Recommended For You