መሰረተ ልማቶችን ቀኝኋላ ሊያዞር የሞከረው ሽብርተኛ

ከሦስት ዓመት በፊት፣ ገንዘብ ሚኒስቴር የግማሽ ዓመቱን የበጀት አፈጻጸም በማስመልከት ማክሰኞ፣ ጥር 28 ቀን 2011 ዓ.ም ሰጥቶት በነበረው መግለጫ፣ ከ102 መሥሪያ ቤቶች የ1000 ፕሮጀክቶችን ዝርዝር ሒደት የሚያሳይ መግለጫ ወይም ፕሮፋይል ተሰናድቶ ከአንድ እስከ ሰባት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ የተጓተቱ ፕሮጀክቶች የ43 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ ማስከተላቸውን አስታውቆ እንደ ነበር አይረሳም። የዚህ ሁሉ ወጪና ክስረት ተጠያቂ ደግሞ ማንም ሳይሆን በወቅቱ አገሪቱን ሲመራና ሙስናን የሥርዓቱ አካል አድርጎ የነበረው መንግሥት፤ የዛሬው ኢትዮጵያን ካላፈረስኩ በማለት የሚቋምጠው አሸባሪ ሕወሓት ቡድን ነው።

በወቅቱ ፣ የተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ መሰረት ያደረገው 102 መሥሪያ ቤቶች 1000 ፕሮጀክቶችን ፕሮፋይል ወይም የአፈጻጸም ወቅታዊ ሒደትን አመላካች ዝርዝር መግለጫዎች ነበር ። የፕሮጀክቶቹ ፕሮፋይል በተዘጋጀበት ወቅት ምን ያህል በጀት እንደተመደበላቸው ፣ መቼ ተጀምረው ማለቅ እንዳለባቸው ወይም እንደነበረባቸው፣ ከተጓተቱም ምን ያህል ወጪ እንዳስከተሉ በተደረገ ማጣራት፣ ከአንድ ዓመት እስከ ሰባት ዓመታት የዘገዩ ፕሮጀክቶች መኖራቸው እንደተደረሰበት በመግለጫው ተካትቶ ነበር።

የወቅቱ የተቋሙ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ይህ የገንዘብ መጠን ለኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በበጀት ዓመቱ ተመድቦለት ከነበረ በጀት (46 ቢሊዮን ብር) ጋር የሚቀራረብ ነው ። በዚህን ያህል ብልሹ አሰራርና ቅጥ ባጣ ስግብግብነት ምክንያት ነበር አገሪቱ መቅኔዋን የተመጠጠችው። ለዚህ ደግሞ የስኳር ፋብሪካዎቹን ብቻ ወስዶ ማየት በቂ ነው ። በዚህም ምክንያት የመንግሥት ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው መርሐ ግብር፣ የጥራት ደረጃ እና በጀት ባለመከናወናቸው በኢኮኖሚ ውስጥ ያመጣሉ ተብሎ የሚጠበቀውን ያህል ውጤት አላመጡም። ለህብረተሰቡ የታለመውን አገልግሎት በመስጠት ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ አልተቻለም።

“እጅግ ዝቅተኛ የፕሮጀክቶች አፈፃፀም ከፍተኛ ለሆነ የመልካም አስተዳደር ችግር መንስኤ ሆኖ ቆይቷል” ከሚለው የፕላንና ልማት ኮሚሽን ሰነድም የምንረዳው ያውና ተመሳሳይ ሲሆን፤ እሱም ከለውጡ በፊት የፕሮጀክቶች አፈፃፀም አዘቅት ውስጥ የነበረ መሆኑን ያሳያል።

ከተለያዩ ተቋማትም መረዳት የሚቻለው ከለውጡ በፊት የነበሩት ቁልፍ ችግሮች ፕሮጀክቶቹ መቼ ተጀምረው እንደሚያልቁ፣ በየዓመቱ ምን ያህል በጀት እንደተጠቀሙ፣ በአካል የሚታየውና በሪፖርት የሚቀርበው አፈጻጸም አለመጣጣም፣ የፕሮጀክት ክትትል ደካማነት ፣ የፕሮጀክቶች ሒደት በማኅደር ተሰንዶ ክትትልና ወቅታዊ ግምገማ አለማድረግ ነበር።

በወቅቱ የጥራት መጓተት፣ ያለ በቂ ጥናትና አንዳንዴም ያለምንም እቅድ ወደ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራ ሲገባ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። በጥናቶቹ ፕሮጀክቶች እንዲገነቡ ከተቋራጮች ጋር የሚገባው ውል ደካማነትም ተጠያቂነት ሲያጓድል እንደቆየ የተመለከተ ሲሆን፤ ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ጋር የተገቡ ውሎች በማሳያነት ቀርበው ነበር። እነዚህን የመሳሰሉ የአሰራር ችግሮች የአፈጻጸም መጓተቶች የሚያስከትሏቸውን ኪሳራዎችና አላስፈላጊ ዕዳዎች ለመቀነስ የመንግሥትን ፕሮጀክቶች ሒደት፣ ትግበራቸውንና የተመደበላቸውን በጀት አጠቃቀምና ሌላውን ዝርዝር ጉዳይ የሚቆጣጠር ተቋም በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር እየተቋቋመ እንደሚገኝ በወቅቱ ተገልጿል። የመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግቦችን ለማሳካት የሚወጠኑና የሚተገበሩ ከመሆናቸው አንፃር ከአገራት የረጅም ጊዜ ወይም የመካከለኛ ዘመን ዕቅዶች የሚመነጩ መሆን እንዳለባቸው ይናገራሉ።

በተጨማሪም መንግሥት የሚያስቀምጣቸውን የልማት ግቦችና አላማዎች ለማሳካት በፕሮጀክቶች አማካኝነት የሚተገበሩ በመሆኑ የፕሮጀክቶች መነሻዎች እና ልየታ እነዚህን ግቦች የሚያሳኩ መሆናቸው በግልጽ በሚያመላክቱ ቁልፍ የውጤት አመላካቾች ሊረጋገጥ ይገባል ። ከለውጡ በፊት በነበረው አስተዳደር የሜጋ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ፣ የተወሰኑ የድርጊት መርሐ ግብሮችን ተግባራዊ ማድረግ ላይ ስለ ሚያተኩረው፣ ስለ “የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት” አይደለም ።

የሜጋ ፕሮጀክቶች ዋና ዋና አገራዊ ፋይዳዎች፤ገንዘብ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፣ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ወደ ሥራ ይገባሉ ተብለው ከሚጠበቁት የኢትዮ ቴሌኮም 40 በመቶ ድርሻን የያዙ ሁለት ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኩባንያዎች፣ በአሥር ዓመታት ውስጥ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይህ እንግዲህ አንዱ ፕሮጀክት ሲሆን ሁሉም በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ ቢጠናቀቁ ኖሮ ምን ያህል ጠቀሜታን ሊያስገኙ እንደሚችሉ መገመት ለማንም አያዳግትም። ከሥራ እድል ባለፈም ከህብረተሰቡ የእለት ተእለት ተጠቃሚነት አኳያ ሜጋ ፕሮጀክቶች ያላቸው ፋይዳ ቀላል አይደለም። ይህንንም በአንድ ተቋም ምሳሌነት ማየት ይቻላል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተፈጥሮ ሃብት፣ መስኖና ኢነርጂ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዱ ዙሪያ ታህሳስ 24 ቀን 2013 ዓ.ም በአዳማ ከተማ የምክክር መድረክ ላይ እንደተገለፀው ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግና አገራዊ የኤሌክትሪክ ሽፋንን ለማሳደግ ‘የብርሀን ለሁሉ’ መርሀ-ግብር ተግባራዊ ተደርጎ እ.ኤ.አ በ2025 ዓ.ም 65 በመቶ የሚሆነው ሕብረተሰብ ከብሔራዊ የኤሌክትሪክ ቋት እንዲሁም 35 በመቶው ደግሞ ከብሔራዊ ግሪድ ውጪ ወይም በኦፍ ግሪድ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል።

የፌዴራል መንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች አስተዳደር እና አመራር ረቂቅ አዋጅን በማዘጋጀት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀረበው የፕላንና ልማት ኮሚሽን በሰነዱ ላይ “የኢትዮጵያ መንግሥት መሰረታዊ የሆኑ አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ ለማድረስ ከፍተኛ ሀብት በመመደብ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ያከናውናል። በተጨማሪም አገራችን ከምትከተለው የልማት አቅጣጫ አንፃር በግሉ ዘርፍ ሊሞሉ የማይችሉ ዘርፎች ላይ መንግሥት በልማት ፕሮጀክቶች አማካኝነት ኢንቨስትመንቶችን እያከናወነ ይገኛል።” ሲል አስፍሯል። ከዚህ መረዳት የሚቻለው ፕሮጀክቶች ለህብረተሰቡ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው መሆኑን ሲሆን ይህንን ኃላፊነት ለመወጣትም መንግሽት ከፍተኛ በጀት መድቦ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአንድ ወቅት የፓርላማ ማብራሪያቸው “ቢሮዎቻችን ሲፀዱ ተንጫጩ፣ አንድነት ፓርክ ሲጠናቀቅም አሽሟጠጡ፣ በሸገርና እንጦጦ ፓርክ ልማትም ተበሳጩ፤ ዳቦ የሚሻ በርካታ ድሃ እያለ የምን ፓርክ እያሉ ተንጫጩ። በአዲስ አበባ የተመዘገበው አስደናቂ ልማት በገበታ ለሀገር በክልሎችም ለመድገም ሲሠራ የውሾቹ ጩኸት ይጨምራል። የብልጽግና ጉዞም ተጠናክሮ ይቀጥላል” እንዳሉት በመሰረተ ልማቱ ዘርፍ ያለው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

መንግሥት ለሚቀጥለው 10 ዓመት የያዛቸውን ዕቅዶች ለመተግበር በሚያደርገው ጥረት ውስጥ መሰረተ ልማት ቁልፉ ጉዳይ ከመሆኑ አኳያ፣ ይህ አሁን እየታየ ያለው ጥረትና ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ የማጠናቀቅ አቅም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል የሚለው የብዙዎች ብቻ ሳይሆን የሁሉም ሰው ፍላጎት ነውና ሁሉም ሊረባረብ ይገባል። ከዚህ አኳያ በአዲስ አበባ ምን እየተሰራ እንደሆን በማሳያነት ወስደን እንመልከት።

የአዲስ አበባ ሜጋ ፕሮጀክቶች አፈጻጸምየአንድ አገር ሁለንተናዊ ጤናማነት ከሚለካባቸው ጉዳዮች አንዱ በሀገር ውስጥ የሚከናወኑት የመሰረተ ልማት ተግባራት ናቸው። በመሆኑም በአገሪቱ መሰረተ ልማቶች አሉ ወይስ የሉም፤ ካሉስ በምን አይነት የእንቅስቃሴ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፤ በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እየሄዱ ነው ወይስ አይደለም? እና የመሳሰሉት ጥያቄዎች መነሳታቸው የግድ ነው ። እነዚህን ጥያቄዎች ታሳቢ በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች በምን አይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ፤ በተለይ “አዲስ አበባ በሽብርተኛው ቡድን ተከባለች” ከሚለው የበሬ ወለደ የጠላት ወሬ አኳያ አንስተን ከአዲስ አበባ ከተማ የሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽሕፈት ቤት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ከሆኑት ከአቶ አዲስ አረጋይ ጋር ቆይታ ያደረግን ሲሆን፤ አጠቃላይ የሜጋ ፕሮጀክቶችን ይዞታና ያሉበትን ሁኔታ እንደሚከተለው ያብራሩታል።

ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት እድሳት ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ በዘመናዊ እና ለሥራ ምቹ በሆነ መልኩ በመከናወን ላይ ይገኛል። 4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞለት እየተከናወነ ያለው የአድዋ ዜሮ ፕሮጀክት የአድዋን ታሪክ ለመዘከር በሚያስችል መልኩ እየተሰራ ነው። 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በጀት 19 ሺህ ካሬሜትር ስፋት ያለውና ከ5ሺህ እስከ 7ሺህ የዲጂታል መጻሕፍት አገልግሎት መስጠት የሚያስችለው የአብርኆት ቤተ መጻሕፍት ግንባታ የፊዚካል ሥራው 95 ነጥብ 5 በመቶ ደርሷል።

የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ለልዩ ልዩ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች አመቺ ሆኖ እየተሰራ ሲሆን፣ በአንድ ጊዜ 1 ሺህ 400 ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚያስችል ዘመናዊ ተሽከርካሪ ማቆሚያና ሌሎች አገልግሎቶችን መስጠት በሚያስችል መልኩ ግንባታው ተጠናቆ በቅርብ ቀን አገልግሎት መስጠት ይጀምራል።

በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ ግንባታው እየተከናወነ ያለው የቤተ መንግሥት የተሽከርካሪ ማቆሚያ ግንባታ ፕሮጀክት አጠቃላይ የግንባታ ክንውኑ 79 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ በአንድ ጊዜ ለ አንድ ሺህ ተሽከርካሪዎች የፓርኪንግ አገልግሎት ይሰጣል። እንዲሁም ሌሎች፣ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞላቸው በመዲናዋ እየተገነቡ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው።

በከተማዋ በግንባታ ላይ ያሉት ሜጋ ፕሮጀክቶችና የልማት ሥራዎች የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህል እና ተፈጥሯዊ ምስህቦችን በጠበቀ መልኩ ነው እየተከናወኑ የሚገኙት ። አዲስ አበባ የአፍሪካ ዋና ከተማ መሆኗንም ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው ።

የአዲስ አበባ ሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሂደት ምንም አይነት መደነቃቀፍ አላጋጠመውም። የሁሉም ሥራ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እየሄደ ነው። አልፎ አልፎ ችግር አጋጠመ ከተባለም የውጭ ምንዛሪ እጥረትና በኮቪድ-19 ምክንያት የሰው ኃይል እንደተፈለገ ማንቀሳቀስ አለመቻሉ ነው። ከዛ ውጪ ከህልውና ዘመቻው ጋር በተያያዘና በጸጥታ ጉዳይ ምንም አይነት ችግር አላጋጠመም።

ሜጋ ፕሮጀክቶቹ እንዳይቋረጡ፣ በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንዲከናወኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቅርብ ክትትልና የምክር አገልግሎት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። ያላሰለሰ ክትትልና ድጋፍ ነው እያደረጉ ያሉት።

ከለውጡ በፊት የነበረው ፕሮጀክቶችን የማጓተት ተግባር፣ እንደ አዲስ አበባ በአሁኑ ሰዓት የለም። በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ አለ። ከለውጡ ወዲህ ተጠናቅቀው ወደ ሥራ የገቡ በርካታ ፕሮጀክቶች ናቸው። አሁን በመጠናቀቅ ላይ ያሉና ወደ ሥራ ለመግባት በዝግጅት ላይ ያሉም አሉ።

አዲስ አበባ ተከባለች፣ የሽብር ቡድኑ እዚህ ደርሷል የሚሉ የሀሰት ትርክቶች ከበሬ ወለደ ወሬነት አልፈው ሥራችን ላይ ያደረሱት ችግር የለም። አብዛኞቹ ሜጋ ፕሮጀክቶቹን እየገነቡ ያሉት የውጭ ዜጎች ናቸው። እንደማንኛው ሰው በግለሰብ ደረጃ ስጋት የተፈጠረባቸው ነበሩ። ነገር ግን ለሁለት ጊዜያት ባደረግነው የጋራ ውይይት መግባባት ላይ የደረስን በመሆኑ ምንም አይነት ችግር የለም። ወሬው በሬ ወለደ መሆኑን በሚገባ አውቀውታል። እዚሁ እየኖሩ ስለሆነም እውነቱ ከእነሱ የተሰወረ አይደለምና ለመግባባት ምንም የወሰደብን ጊዜ የለም። የሥራ ገንዘብ የሚላክላቸው በባንኮቻቸው በኩል ስለሆነም አገሮቻቸውም አዲስ አበባ ውስጥ ባለው ሰላም የተማመኑ ስለመሆናቸው በቂ ማሳያ ነው።

እዚህ ላይ ማሳሰብ የሚያስፈልገው የከተማው ነዋሪ በሚነዛው የሀሰት ወሬ ምንም ሳይረበሽ ሥራውን እንደተለመደው በተረጋጋ መንገድ ሊያከናውን የሚገባው መሆኑን ነው። የሽብር ቡድኑ የከፈተብንን ጦርነት በድል አጠናቅቀን ወደ ተለመደው መደበኛ ሰላምና ሥራችን እስከምንመለስ ድረስ ህዝቡ ከመንግሥትና ከመከላከያ ጎን በመቆም ይህንን ከልማታችን ሊያደናቅፈን፣ አገራችንን ሊያፈርስ የተነሳን አሸባሪ ኃይል ማጋለጥ፤ አካባቢውን በንቃት መጠበቅ ይገባዋል።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ኅዳር 25/2014

Recommended For You