ከጅብ ጋር እየተጋፉ፣ ቅጠል ለቅመው በመሸጥ ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩት መነኩሴ

እማሆይ ሙሉዓለም ፈረደ ይባላሉ። አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ፈረንሳይ ኬላ አካባቢ ነዋሪ ናቸው። እንጨት ለቅሞ፣ ቅጠል ጠርጎ በመሸጥ እራሳቸውን እና አምስት ቤተሰብ የማስተዳደር ኃላፊነት ወድቆባቸዋል። በዚህ ስራ ወደ እንጦጦ ሲያቀኑ፣ በአጋጣሚ ከጅብ ዋሻ ገብተው በተዓምር መትረፋቸውን ይናገራሉ። ኑሯቸው ዛሬም ካለበት ፈቅ ባይልም አሁን በሕይወት ያሉት ሦስቱን ልጆችና አንዲት የእህታቸውን ልጅ ለማሳደግ የተለያዩ የጉልበት ሥራዎችን በመሥራት በሕይወት ሲፈተኑ ቆይተዋል። በባሬላ አሸዋ እስከ ማጋዝ፣ በጭንቅላታቸው ድንጋይና በጀርባቸው ሲሚንቶ እስከ መሸከም ደርሰዋል። አሁንም የህይወት ፈተናቸው አላቆመም። ‹‹ምነው ባልተወለድኩ በቀረብኝ›› ብለው ወደዚህ ዓለም በመምጣታቸውም እስኪማረሩ ድረስ ሕይወት በብርቱ እየተፈታተነቻቸው ትገኛለች።

እማሆይ ሙሉዓለም አሁን ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ይሁኑ እንጂ ተወልደው ያደጉት ሰሜን ጎንደር ደባርቅ ወረዳ ውስጥ ነው። አባታቸው በአንባ ጊዎርጊስ ቤተክርስቲያን አካባቢ በሚኖሩ ነዋሪዎች የታወቁና በበጎነታቸው የተወደዱ የዳባት ወረዳ ተወላጅ ነበሩ። እናትና አባታቸው ተጋብተው እሳቸውን እስኪወልዱና እስኪሞቱ ጥሩ ሀብት ነበራቸው። ሀብታቸው ከራሳቸው አልፎ ዝቅተኛ ኑሮ ላላቸው ሁሉ የሚተርፍ ነበር። ድል ባለ ሠርግ ድረዋቸውም በ14 ዓመታቸው የመጀመርያ ልጃቸውን ለመውለድ በቅተዋል።

ሆኖም የእሳቸውን ዕድሜ ያህል በሚበልጣቸውና ወላጆቻቸው በመረጡላቸው ትልቁ ባለቤታቸው ደስተኛ አልነበሩም። እጅግ ቀናተኛ በመሆኑም ያለ ፈቃዱ የሚያንቀሳቅሳቸውም አልነበረም። ሁለቱም ወላጆቻቸው ያረፉት በዚህ ደስተኛ ባልነበሩበት ወቅት ነው። የወላጅ ሞትና የትዳር አለመመቸት ተስፋ አስቆረጣቸው። በ17 ዓመታቸው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ገዳም ሰፈር ያለችው የእናታቸው እህት አክስታቸው ጋር ልጃቸውን ለአባቱ ጥለው ነጠላቸውን ብቻ አንጠልጥለውና ከባለቤታቸው ጠፍተው ለመምጣት ሲወስኑ የራሳቸውንም ሆነ የወላጆቻቸውን ሀብት ዞር ብለው አላዩም።

ለትራንስፖርት ብለው በመሐረባቸው በቋጠሯት ጥቂት ብር እስከ ባህር ዳር በ14 ብር መጡ። በቀረችው ደግሞ እስከ አዲስ አበባ ዘለቁባት። የቀለም ትምህርትም ሆነ በባልና በወላጅ ቁጥጥር ከመተዳደር አልፎ እንብዛም የሕይወት ተሞክሮ ያልነበረው የታዳጊነት ዘመናቸው አዲስ አበባ ከተደረሰም ሆነ በጉዞ ላይ አክስታቸውን እስኪያገኙ ለምግብና ለመኝታ ሊያወጡት የሚችሉትን ወጪ አስቀድሞ አላስገነዘባቸውም።

አልታደልኩም የሚሉት እማሆይ ሙሉዓለም ፈተናቸው ከዚሁ ጀመረ። የቋጠሯት ጥቂት ሳንቲም በማለቋ ጉዞ ላይ ረሃብና ውሀ ጥም በብርቱ ፈተናቸው። መኪና ውስጥ ተሳፋሪዎች የሚያጋሩትን ቆሎ ቀማምሰው ሲያስታግሱት ቆዩ። ከረሃባቸው ለዘለቄታው ለመዳንና ከድካማቸው ለማረፍ አክስታቸውን ተስፋ አድርገው አዲስ አበባ ደረሱ። እግር በእግር ተከትሏቸው፣ ከመጡበት መኪና ውስጥ ተሸሽጎ፣ በተሳፋሪዎች እንክብካቤ እየተደረገለት የቆየው የአራት ዓመቱ ህፃን ልጃቸው ባልጠበቁት ሁኔታ ቀሚሳቸውን አፈፍ አድርጎ አብሮ የወረደውም በዚሁ ጊዜ ነው። ከማይመለሱበት ቤት በመምጣቱ ቢደሰቱም የት እንደሚያደርጉት ግን አሳስቧቸው ነበር።

እለቱን ብቻ ሳይሆን ለዘለቄታው ከአክስታቸው ጋር ለመኖር ማሰቡ ጉልበት ሆኗቸው ነበር ገዳም ሰፈር የደረሱት። ነገር ግን እንዳሰቡትና እንደተመኙት አልተሳካላቸውም። ከነልጃቸው ረሃብና ጥማቸውን ከመጥላት እንዲሁም የተመቸ አዳርና እረፍት ከመመኘት አልፈው ቀጣይ ዘመናቸውን አብረዋት ለመኖር ያለሙት አክስታቸው ቤት ሲዘልቁ ጎረቤቶቿ ካረፈችና ከተቀበረች ሳምንታት ማለፋቸውን አረዷቸው። ወይ ከትዳራቸው ወይ ከአክስታቸው ሳይሆኑ መቅረታቸው ብርቱ ስጋት ውስጥ ከተታቸው።

በተለይ የህፃን ልጃቸው የወደፊት ዕጣ ፈንታ የአክስታቸው ሞት፣ ድንጋጤና ስኬታማ አለመሆናቸው ተደማምሮ ከባድ ሀዘን ውስጥ ከተታቸው። ያክስታቸውን ጎረቤቶች እጅግ ባሳዘነና እንባ ባራጨ ሁኔታ በምሽት እርማቸውን ካወጡ በኋላ የአክስታቸውን ቤት ቀበሌ ለሌላ ሰው ስለሰጠው ማደርያ መፈለግ ነበረባቸው። የአክስታቸው ጎረቤቶች ይሄንኑ አስረዷቸው። ይሄን ዜና መስማት እንኳን ሰፊ ከተማ በሆነችውና በሕዝብ ብዛት በተጥለቀለቀችው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሆኖ በሌላ ጠባብ ከተማ ውስጥ ሆኖም ለከፋ ራስ ምታት ይሰጣል። የቀለጠ መንደር በመሰለችው ገዳም ሰፈር ውስጥ በተገኙበት ምሽት ወቅት የሰሙ መሆኑ ደግሞ ግራ ከመጋባት አልፎ አእምሮ አውኳቸው ነበር።

ይኼ ሁሉ ምግብ ካለመቅመሳቸው ጋር ተዳምሮም አጥወልውሎ አዞራቸው። የሚያደርጉትንም አሳጣቸው። ብዙዎቹ ለቅሷቸውን ሰምተው የተሰበሰቡት የአክስታቸው ጎረቤቶች እቆሙበት ትተዋቸው ወደዬቤታቸው ገቡ። ለግላጋ ቁመናቸውን፣ መልከ መልካምነታቸውንና ታዳጊነታቸውን ያዩት ጥቂቶቹ ደግሞ እኔ ጋር ትዳር፤ እኔ ጋር ትሁን እያሉ ተሻሙባቸው። በግርግሩ መካከል እንደታዘቡት ልጃቸውን ጠልቶ እሳቸውን የወደደው ብዙ ነበር።

በወቅቱ ሁኔታው ባይገባቸውም እስከ መሰዳደብም ደርሰውባቸዋል። ሆኖም አንዲት ሲያዞራቸው ደግፈው ውሃና ምግብ ያቀረቡላቸው ጠና ያሉ መልካም ሴት ኮስተር ብለው ከእሳቸው በቀር ማንም ጋር እንደማያድሩና ሲነጋ ቤተሰቦቻቸውን ፈልገው እንደሚያስረክቧቸው ተናገሩ። ሴቲቱ ተሰሚነት በማግኘታቸው ሌሎቹን በዚሁ ተገላገሏቸው።

ኋላ እንደነገሯቸው ከእኔ ጋር ትሁን የሚለው ወከባና ግርግሩ በሴት አዳሪነት የማሰማራት ጽዩፍ ዓላማ ያለው ነበር። ልጃቸውን ጠልተው እሳቸውን የወደዱበት ምክንያትም ይሄው ነበር። ልጅ ያላት ሴት ብዙ ጊዜ ልጇ ሥራ ለመሥራት ስለማያስችላት በሴት አዳሪነት እንድትሰማራ አይፈለግም። መልካሟ ሴት ከነልጃቸው የተወሰኑ ቀናት አስቀምጠው እያበሉና እያጠጡ የእናትነት ምክራቸውን ሲለግሷቸው ቆዩ። የፈለገው ነገር ቢሆን በእግዚአብሄርም፤ በሰውም ዘንድ አስነዋሪ በሆነው በሴት አዳሪነት ተግባር እንዳይሰማሩም አስማሏቸው። አዲስ አበባ ላይ ከገጠር ሚመጡ ሴት ልጆችን በዚህ ተግባር ማሰማራት እራሱን እንደቻለ የገቢ ምንጭ መቆጠሩን በደንብ አድርገው አስገነዘቧቸው።

‹‹ሴቲቱ ስለሴት አዳሪነት ጥሩ ግንዛቤ ሰጡኝ። አብዝቼ እንድጠየፈውም አደረጉኝ። ባለቤቴ ህፃናት ልጆችን እርግፍ አድርጎብኝ ሲሞት እንኳን፤ ሰዎች ወርቅ አለሽ፣ ልብስ አለሽ፣ ቆንጆ ነሽ ለምን አትተዳደሪበትም ሲሉኝ ድንጋይ መሸከምና ልጆቼን ማስተማርና ማሳደግ እንጂ ሴት አዳሪ መሆን አልመረጥኩም። አሁን ድረስም ሌሎች ሴቶች እንዲጠየፉት እያደረግኩ እኖራለሁ›› ብለውናል።

እማሆይ ሙሉዓለም ታሪካቸውን ቀጥለው እንዳወጉን ታድያ መልካሟ ሴት ለአንድ ሰው ተድረው እራሳቸውን ችለው ከቤታቸው እንዲወጡ አደረጓቸው። ከእኝህ ሰው ሦስት ልጆች አፍርተዋል። በህፃንነታቸው ለማያውቁት ሰው ተድረው በ14 ዓመታቸው ከወለዱት አንድ ወንድ ልጅ ጋርም የአራት ልጆች እናት ለመሆን ቻሉ።

ባለቤታቸው የመንግስት ሠራተኛ ነበሩ። መልካም በመሆናቸውና ደሞዛቸውን ተቀብለው ስለሚሰጧቸው በቤታቸው ውስጥ ምንም ችግር አልነበረም። ሁሉ የተሟላ ነበር። ጥሩ ፍቅር የነበራቸውና እርስ በእርስ የሚዋደዱም ነበሩ።

እማሆይ ሙሉዓለም አሁንም ገደቢሱ ዕድላቸው ባለቤታቸውን በሞት ሲነጠቁ ትዳራቸውንና የተደላደለ ኑሯቸውን አፈረሰው። ሦስት ህፃናት ልጆቻቸውን አራግፈውባቸው በመሆኑ የመከራው ቀንበር በእጅጉ ከበደባቸው። አንዲት አካል ጉዳተኛ የእህታቸውን ልጅ ከገጠር አምጥተው ያሳድጉም ነበርና እራሳቸውን ጨምሮ ስድስት ቤተሰብ መምራት ተሳናቸው። በሟች ባለቤታቸው የጡረታ ገንዘብ ህፃናት ልጆቻቸውን ማሳደግና ማስተማር ቢፈልጉም ባለቤታቸው ለ17 ዓመታት ይሰሩበት የነበረው የህንፃ ኮንስትራክሽን አልፈቀደላቸውም።

<<ክስ የመመሥረት ዕውቀቱም ሆነ ጊዜውም አልነበረኝ። ልጆቼ በአናት በአናቱ የተወለዱ ትናንሾች ስለነበሩ ያገኘሁትን የጉልበት ሥራ መሥራት ጀመርኩ። ጎበዝ ነበርኩ እንደዛሬ አቅሜ አልደከመም። መንገድና ቤት ሲሠራ ድንጋይ፣ ሲሚንቶ እሸከማለሁ። ለሁለት ሆኜ አሸዋ በባሬላ አግዛለሁ>> ሲሉ የልጆቻቸውንና የራሳቸውን ሕይወት ለማቆየት በድካም ሲታትሩ የቆዩበት ሁኔታ ወደኋላ መለስ ብለው አስታውሰውታል።

‹‹ከዚህ በኋላ ነው ለሰፈሬ ቅርብ ወደ ሆነው እንጦጦ ጋራ ወጥቼ ጀርባዬ እኪጎብጥ እንጨት ሸከማ የጀመርኩት›› ሲሉም በእነዚህ ስራዎች ተሰማርተው ለ13 ዓመታት እንደ እናትም እንደ አባትም ሆነው ልጆቻቸውን እየተንከባከቡ ሲያስተምሩ መቆታቸውን የገለፁት። ትልቁ ልጃቸው በፊናው እየተሯሯጠ ሲያግዛቸው ኖሯል። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ታሞ ሞተባቸው።

እንዳጫወቱን ሴቷ ልጃቸው ጎበዝ ነበረች። በ13 ዓመት ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ ወድቃ 12ኛ ክፍልን አጠናቀቀችላቸው። ውጤት ቢመጣላትም የተማርኩበትን ያህል ስራ ገብቼ እናቴን እረዳለሁ በማለት ታይፕ ተምራ ሥራ ገባች። ነገር ግን ትንሽ እንደሰራች አሰሪዎቿ ዋስ አምጪ ብለው አባረሯት። ዋስ የሚሆናት ዘመድ በማጣታቸው አሁን ላይ አግብታ ሁለት ልጆች ወልዳለች። ባሏ ሥራ ስለሌለው እናቱ በገንዘብ እየደጎሙት ነው የሚኖረው። ስለሆነም ልጃቸው ራሷን አልቻለችላቸውም።

ሁለቱ ወንዶች ልጆቻቸው፤ የሴቷ ታናሽ ዘጠነኛ፣ የመጨረሻው ደግሞ ሰባተኛ ክፍል ደርሰዋል። እዚህ መድረስና የቻሉት በየክፍሉ ሁለቴና ሶስቴ እየደጋገሙ ሲሆን ትምህርታቸውን ያቋረጡትም እዚሁ ደረጃ ላይ እንደደረሱ ነው። ቢቸግራቸው ትልቁ ልጃቸውን የሹፍርና ሙያ አስተምረውታል። ሆኖም አልፎ አልፎ የሚያሰራው ሰው ቢኖርም ዋስ በማጣቱ ምክንያት በቋሚነት ተቀጥሮ መሥራት ባለመቻሉ በእናቱ ከመጦር አልዳነም።

ለእማሆይ ሙሉዓለም ቅጠል ሽጠው በሚያገኟት ሣንቲም የልጆቻቸውንና የራሳቸውን ሕይወት የሚገፉበት የአዲስ አበባ ከፍተኛ ቦታ – እንጦጦ – ልዩ ትርጉም አለው። ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከአንኮበር መጥተው አዲስ አበባን ሲቆረቁሩ ያረፉበትን እና ቤተ መንግስታቸውን የሰሩበትን ይህን ታሪካዊ ቦታ እማሆይ ሙሉዓለም ሰርክ ማልደው ሥራቸውን ያከናውኑበታል።

ከፈረንሳይ እንጦጦ አሥሬ ከመመላለስ ሦስት አራት ሰው የሚይዘውን እንጨት በመስበር በጀርባቸው ተሸክመው በአድካሚና አሰልቺ ረጃጅም ሰንሰለታማ ተራራው እንደ ዘበት ሲመላለሱበት ኖረዋል። አሁን ላይ ከጉዳት ጋር ተያይዞ ጉልበታቸው በየጊዜው በሚያማቸው ህመም ምክንያት በመድከሙና ዕድሜያቸውም እየገፋ በመምጣቱ በብዛት የረገፈ ቅጠል ጠርገው ወደ ፈረንሳይ ሰፈር በማምጣት እየቸረቸሩ በመሸጥ ኑሯቸውን እየገፉ ይገኛሉ።

እማሆይ ገጠመኛቸውን እንዳጫወቱን ታድያ ባለፈው ዓመት መጨረሻ እንደልማዳቸው ማልደው ርዝመቱ ከባህር ወለል በላይ 3 ሺህ 200 ሜትር በሆነው በዚህ የአንጦጦ ሰንሰለታማ ተራራ አንድ ክፍል የረገፈ ቅጠል ይጠርጋሉ። አንዲት ሴትም አብራቸው እየጠረገች እንደነበረች ያስታውሳሉ። ጨለማው ለንጋቱ ገና ቦታውን እየለቀቀ በመሆኑ ቅጠሉን እየጠረጉ ሳያስቡት ጅብ ዋሻ ይገባሉ።

‹‹ጅቡ አፈጠጠብኝ። ደርቄ ቀረሁ። መናገር ሁሉ አቃተኝና በድንጋጤ ለሀጬ ተዝረበረበ። በዚህ ድንጋጤ ውስጥ ሆኜ የገባሁበት የጅብ ዋሻ እንደመሆኑ ካፈጠጠብኝ ትልቅ ጅብ ጀርባ ሌሎች ብዙ ጅቦች እንደሚኖሩና እንዴት አድርገው ሊበሉኝ እንደሚችሉ አስብ ነበር። የቀረኝ ከአሁን ከአሁን ተከመረብኝ የሚለውን በሆዴ ማሰብ ብቻ ነው እንጂ እንደሚበላኝ እርግጠኛ ነበርኩ›› ይላሉ አሁን የሆነ እየመሰላቸውና ሰውነታቸውን ድንጋጤ እየወረረው።

ጅቡ አብራቸው ቅጠል ትጠርግ የነበረችውን ሴት አላያትም። ሆኖም የጅቡንና የእሳቸውን ሁኔታ ያስተዋለችው ይህች ሴት ራቅ ብላና ተንበርክካ ጅቡን እንደለመነችላቸውና ዕይታውን ከእሳቸው ላይ ነቅሎ ወደ እሷ እንዲያሳርፍ እንዳደረገችውም ነግረውናል። ከዚህ በኋላ የሆነውን አያስታውሱም። ልጆቻቸው ቦታው ድረስ ተጠርተው ተላቅሰው በቃሬዛ መነሳታቸውን የሰሙት ሦስት ወር ተኝተው በመታከም ካገገሙና እራሳቸውን ካወቁ በኋላ ነበር።

ሕክምናው በዚህ ሁኔታ የጠረጉትን ቅጠል ሸጠው ለክፉ ቀን በማለት የቋጠሩትን የ10 ሺህ ብር ጥሪት አሟጧል። ምኒልክ ሆስፒታል ገንዘባቸው ሲያልቅ ባይድኑም አስወጥቷቸዋል። የጤና መድህን ካርድ ለማውጣት ገንዘብ ስላጡ በተመጣጣኝ ዋጋ መድሃኒት መግዛት አልቻሉም። በቅርቡ አንድ ሺህ ብር የተባሉትን መድሃኒት አንዲት መደብሩ ላይ ስትገዛ ያገኝዋት መልካም ሴት ከኪሷ 500 ብር፣ ተጨማሪ 500 ብር ደግሞ ነጠላዋን አንጥፋ በመለመን ነበር መድሃኒቱን ገዝታ የሰጠቻቸው።

በህመማቸው ምክንያት ከሦስት ወራት በፊት ቅጠል ጠረጋውን በማቆማቸው ለዕለት ጉርስና ለመድሃኒት መግዣ ቤተክርስቲያን ደጃፍ ቁጭ ብለው እስከ መለመን ደርሰዋል። እማሆይ ሙሉዓለም አሁን ላይ ወደ መደበኛ ቅጠል ጠረጋ ሥራቸው መመለሳቸውን በማካፈል ጨዋታቸውን ቋጭተውልናል።

እኛም የእንጦጦ ፓርክም ሆነ በሸክላና በሌሎች የእጅ ጥበብ ሙያዎች የተደራጁ የቀድሞ የእንጦጦ እንጨት ተሸካሚ ሴቶች ማህበራት፣ በተለይም ቤተክርስቲያናት እንዲህ እንደ እማሆይ ሙሉዓለም ያሉ ደካማ እናቶችንና ልጆቻቸውን በማካተት የሚደግፉበት አሠራር ቢያመቻቹ የደካማ እናቶችንና ልጆቻቸውን ሕይወት መታደግ እንደሚቻል በመጠቆም ጽሑፋችንን ደመደምን።

ሠላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ኅዳር 25/2014

Recommended For You