ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በነገው የቫሌንሲያ ማራቶን ለድል ይጠበቃሉ

በተለያዩ የዓለም ከተሞች ከሚካሄዱት ታላላቅ የማራቶን ውድድሮች መካከል የዓመቱ የመጨረሻው ውድድር ነገ በስፔኗ ቫሌንሲያ ከተማ ይደረጋል፡፡ በዓለም ኤትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ ከተሰጣቸው ሰባት የማራቶን ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው የቫሌንሲያ ማራቶን እአአ በ1981 መካሄድ የጀመረ ሲሆን ዘንድሮ ለ41ኛ ጊዜ ይደረጋል፡፡ ነገ በሚካሄደው ውድድር ላይም 18ሺ ሯጮች እንደሚሳተፉበት የዓለም አትሌቲክስ በድረገጹ አስነብቧል፡፡ በአውሮፓ ተወዳጅ ከሆኑት ማራቶኖች መካከል አንዱ በየሆነው ይህ ውድድር እጅግ ታዋቂ የሆነበትን የግማሽ ማራቶን ሩጫ በቅርቡ ማካሄዱ የሚታወስ ነው፡፡

በዚህ ውድድር በርካታ ፈጣን ሰዓት ያላቸው አትሌቶች የሚካፈሉ ቢሆንም በርቀቱ የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ በሚታወቁት ጎረቤታሞቹ አገራት የኬንያ እና ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች አሸናፊ ይሆናሉ በሚል ከስፖርት ቤተሰቡ ቅድመ ግምት አግኝተዋል፡፡ በቦታው ሁለቱም ጾታዎች የክብረወሰን ባለቤት የሆኑት ኬንያዊያን ሲሆኑ፤ ፈጣኑን ሰዓት ያስመዘገቡትም ባለፈው ዓመት በተካሄደው ውድድር ነው፡፡ በሴቶች ፔሬስ ጄፕቺርቺር 2:17:16 በሆነ ሰዓት በመግባት ክብረወሰኑን ስታሻሽል፤ በወንዶች ደግሞ ኢቫንስ ቼቤት 2:03:00 የሆነ ሰዓት አለው፡፡ በነገው ውድድር ላይ የሚካፈሉ ታዋቂ አትሌቶችም በወንዶች ከ2 ሰዓትከ03 ደቂቃ በታች የሆነ ፈጣን ሰዓት ሲኖራቸው፤ በሴቶች ደግሞ ከ2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ በታች የሆነ ሰዓት ያስመዘገቡ አትሌቶች ይፎካከራሉ፡፡

በሁለቱም ጾታዎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚካፈሉ ሲሆን፤ በወንዶች ሙሌ ዋሲሁን፣ ጌታነህ ሞላ፣ ክንዴ አጥናው፣ አንዱአምላክ በልሁ ለአሸናፊነት ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ከሚጠበቁት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ሰፊ ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል ክንዴ አጥናው እአአ የ2019 ቫሌንሲያ ማራቶን አሸናፊ መሆኑ ለአሸናፊነት እንዲጠበቅ አድርጎታል፡፡ ወጣቱ አትሌት በወቅቱ ርቀቱን እጅግ ፈጣን በተባለ ሰዓት ሲሸፍን ያጠናቀቀው በ2.03.51 ሰዓት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በቀጣዩ ዓመት ዳግም አሸናፊ ይሆናል በሚል ቢጠበቅም ውጤታማ ሊሆን አልቻለም፤ በነገው ውድድር ላይም ወደ ስኬቱ ሊመልሰው የሚችል ብቃት እንደሚያሳይ ይጠበቃል፡፡

ሌላኛው 2.03.16 የሆነ የግሉ ፈጣን ሰዓት ያለው ሙሌ ዋሲሁንም ለአሸናፊነት ከሚጠበቁት አትሌቶች መካከል ተካቷል፡፡ በአምስተርዳም፣ ለንደንና የዱባይ ማራቶኖች ተሳትፎ ያለውና በትልልቅ ውድድሮች ተሳትፎ ልምድ ያካበተ አትሌት እንደመሆኑ በቫሌንሲያ የተሻለ ውጤት ሊያስመዘግብ ይችላል በሚል በስፖርት ቤተሰቡ ይጠበቃል፡፡ በመምና በጎዳና ላይ ሩጫዎች የሚታወቀው አትሌት ጌታነህ ሞላም በውድድሩ ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ነው፡፡ አትሌቱ እአአ 2019 በዱባይ ማራቶን አሸናፊ ሲሆን ያስመዘገበው ፈጣን ሰዓት 2.03.34 ነበር፡፡ በግማሽ ማራቶን ሩጫ የሚታወቀው ሌላኛው አትሌት አንዱአምላክ በልሁም በዚህ ማራቶን ተሳታፊ እንደሚሆን ታውቋል፡፡

በኬንያዊያን በኩል የውድድሩ አሸናፊ ይሆናል በሚል ላውረንስ ቼሮኖ ይጠበቃል፡፡ አትሌቱ ባለፈው ዓመት በዚህ ውድድር ላይ ተሳትፎ ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ፤ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ተሳትፎው አራተኛ በመሆን ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው፡፡ ከኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ባሻገር ከፍተኛ ተፎካካሪው እንደሚሆን የሚጠበቀው የአገሩ ልጅ ጄኦፍሪ ካምዎረር የውድድሩ ተሳታፊ የሚሆን አትሌት ነው፡፡ በተከታታይ ለአራት ዓመታት የኒውዮርክ ማራቶን አሸናፊ የሆነው ይህ አትሌት በሌሎች ታላላቅ ማራቶኖች ላይም ያለው ተሳትፎ ውጤታማ ሊያደርገው እንደሚችልም ተገምቷል፡፡

በሴቶች በኩልም በተመሳሳይ ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ለድል የሚጠበቁ ሲሆን፤ ከተወዳዳሪዎቹ መካከል ፈጣን ሰዓት ያላት ጉተኒ ሾኔ ቀዳሚውን የአሸናፊነት ቅድመ ግምት አግኝታለች፡፡ አትሌቷ ባለፈው ዓመት በዱባይ 2.20.11 የሆነ ምርጥ ሰዓቷን ስታስመዘግብ፤ በዚህ ዓመትም በተሳተፈችባቸው ውድድሮች ጥሩ አቋም ማሳየት ችላለች፡፡ በርቀቱ ሰፊ ልምድ ያላት ይህች አትሌት ኦታዋ፣ ሴኡል እና ሴቪሊ ማራቶኖች በተለይ ትታወቃለች፡፡ በአምስተርዳም፣ ፓሪስ፣ ቶኪዮ እና ሚላን ማራቶኖች ተሳትፋ በርቀቱ ልምድ ያካበተችው ሌላኛዋ አትሌት አዝመራ ገብሩም የውድድሩ ተጠባቂ አትሌት ሆናለች፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ኅዳር 25/2014

Recommended For You