ለአገራዊ ጥሪው አገራዊ ምላሽ

ኢትዮጵያ በየዘመኑ የተነሱባትን የውስጥ ባንዳንና የውጭ ወራሪ ኃይሎችን በማሳፈር አይቀጡ ቅጣት ቀጥታ በመጡበት መልሳለች። ለዚህም አጥፊዎቿን አጥፍታ ወራሪዎቿን አሳፍራ የመለሰችባቸው ታሪኮቿ ምስክር ናቸው። በታሪኮቿ ሁሉ ኢትዮጵያ አሸናፊ ለመሆን የበቃችው ካልነኳት የማትነካ፤ የራሷን አሳልፋ የማትሰጥ፤ የሰውንም የማትሻ ኩሩ አገር በመሆኗ እንዲሁም እውነትን ብቻ ይዛ ስለምትቆም ነው።

ዛሬም ቢሆን ከአብራኳ የወጡ ልጆቿ ጡት ነካሽ ሆነው ከጀርባ ወግተው አቁስለው ቢያደሟትም፣ እውነቷን ነጥቀው ቢክዷትም እውነት ትመነምናለች እንጂ አትበጠስም እንዲሉ ኢትዮጵያ እውነቷን ይዛ ታሸንፋለች። አሸናፊነት፣ ጀብደኝነት አዲስ ታሪኳ ያልሆነች ኢትዮጵያ በተለይም እንደ ሕዝብ በአንድነትና በጋራ በመቆም ሉዓላዊ ክብሯን ሊያዋርድ፣ ሊደፍሯትና ሊያፈርሳት የመጣን ወራሪ ኃይል በቆፈረው ጉድጓድ ቀብራ ትንሳኤዋን ለማረጋገጥ ጫፍ ደርሳለች።

ኢትዮጵያ ተገዳ በገባችበት የመኖር ወይም ያለመኖር ጦርነት ኢትዮጵያውያን በሁሉም ግንባር በመሰለፍ ስኬታማ እየሆኑ ይገኛሉ ። ጦርነቱ ሁለንተናዊ እንደመሆኑ ሕዝቡ አካባቢውን በንቃት ከመጠበቅ አንስቶ አውደ ውግያው እየተካሄደ ባለበት ግንባር ድረስ በመሰለፍ ድል እያስመዘገበ ይገኛል ። በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የህልውና ጦርነቱን ግንባር ሄደው ለመምራት ወስነው በተግባርም ግንባሩን ከተቀላቀሉበት ማግስት ጀምሮ ጀግናው የኢትዮጵያ ሠራዊት ድርብ ድርብር ድሎችን በማስመዝገብ ስኬታማ መሆን ችሏል።

ጦርነቱን በስኬት ለማጠናቀቅ እንዲቻል የጀርባ አጥንት የሆነውን ኢኮኖሚ በጥንቃቄ መምራት ተገቢ ስለመሆኑ ብዙዎች ያነሳሉ። ምክንያቱም ጦርነቱ እየጠየቀ ያለውን ከፍተኛ ወጪ በአግባቡ መመለስ ካልተቻለም የጦርነቱ ድል ይርቃል። በዚህም መላው የአገሪቱ ሕዝብ በአንድም በሌላ ተጎጂ ይሆናል። ለዚህም ከመንግሥት ባለፈ ሕዝቡ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት ይታመናል። በአሁኑ ወቅትም ከትልቅ እስከ ትንሽ፤ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአይነትና በገንዘብ ድጋፍ እያደረገ የሚገኘውም ለዚሁ ነው። ማህበረሰቡ እያደረገ ያለው ድጋፍ ለሠራዊቱ አቅም፣ ጉልበትና ብርታቱ እንዲሁም የሞራል ስንቁ ነው።

ጦርነት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ የሚያስከትል እንደመሆኑ በተለይም ኢኮኖሚው ጦርነቱን መሸከም እንዲችል በርካታ ሥራዎች መሠራት ይኖርባቸዋል። የሚሠሩ ሥራዎች በሙሉ ለመንግሥት ብቻ የሚተው እንዳልሆነና እያንዳንዱ ዜጋ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበትም ብዙዎች ያነሳሉ ። ነባራዊ ሁኔታውም የሚያሳየው ይህንኑ ነው ። ጦርነቱ የሚጠይቀው ወጪ ከፍተኛ እንደመሆኑ በመንግሥት ብቻ የሚሸፈን አይደለም ። እስካሁን ባለው ሂደትም ማህበረሰቡ የጎላ ተሳትፎ በማድረጉ ጦርነቱ የሚያስከትለውን ኢኮኖሚያዊ ጫና መቋቋም ተችሏል።

ጦርነቱን ለማሸነፍ ኢኮኖሚውን ማሸነፍ አማራጭ የሌለው ጉዳይ በመሆኑ እያንዳንዱ ዜጋ በኢኮኖሚው ዘርፍ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ወገንተኝነቱን እያረጋገጡ ይገኛሉ። ይሄ ባይሆን ኢኮኖሚውም ጦርነቱን መሸከም ያቅተውና ይንገዳገዳል ። የተናጋው ኢኮኖሚም ማህበራዊ ቀውስን በመፍጠር ሰላማዊ ሕይወትን መምራትም ሆነ ጦርነቱን ማካሄድ ፈታኝ ይሆናል። ኢኮኖሚ ሁለተኛው የጦር ግንባር ነው የሚባለውም ለዚሁ ነው።

ሁለተኛው የጦር ግንባር ላይ እያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነቱን መወጣት ካልቻለ ጦርነቱን ማሸነፍ አይቻልም። የሕዝብ ወገንተኝነትና ድጋፍ አሁን ለገባንበት ጦርነት መውጫ መንገድ ነው። ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁኑ ወቅት በየአካባቢው ከሚደረገው የሥንቅ ዝግጅት በተጨማሪ በተለያዩ ተቋማትና የግል ባለሃብቶች ከፍተኛ ድጋፍ እየተደረገ የሚገኘውም ለዚህም ነው። ሕዝቡ በየደረጃው እያደረገ ያለው ድጋፍ ጦርነቱን ባጠረ ጊዜና ስኬታማ በሆነ መንገድ ማጠናቀቅ እንዲቻል ያለው አበርክቶ የጎላ ነው።

ከሰሞኑም የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል። ቃል የተገባው ገንዘብም በቅርቡ ገቢ የሚደረግ መሆኑን የኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ ትምህርትና የቴክኒክ ሙያ ተቋማት ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ሞላ ጸጋዬ ገልጸዋል።

አገሪቷ ወደ ጦርነት ከመግባቷም አስቀድሞ በተለያዩ ወቅቶች የገጠሟትን ፈተናዎች መሻገር እንድትችል በማህበሩ አቅም እንዲሁም ተቋማቱን በማስተባበር ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ያነሱት ዶክተር ሞላ፤ አሁንም ቢሆን ጦርነቱ የመኖርና ያለመኖር እንደመሆኑ አገራዊ ለሆኑ ጥሪዎች ምላሽ መስጠት የግድ ነው። አገር ከሌለ ምንም ሊኖር አይችልም። ሠርቶ ማግኘትም ሆነ ነግዶ ማትረፍ የሚቻለው አገር ሰላም ውላ ሰላም ማደር ስትችል መሆኑን በመገንዘብ ተቋማቱ ባለ አቅማቸው ሁሉ ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ በማድረግ ወገንተኝ ነታቸውን እያሳየ ይገኛል።

የትምህርት ተቋማቱ በአሁኑ ወቅት እያደረጉ ያለውን አገራዊ ድጋፍ ከወትሮው ለየት የሚያደርገው በትምህርት ሚኒስቴር የሥራ አመራር ቦርድ አማካኝነት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማህበር ለአገራዊ ጥሪው ምላሽ እንዲሰጥ ማድረጉ ነው። ማህበሩም የተሰጠውን አቅጣጫ መሠረት በማድረግ ሁለት ውሳኔዎችን አሳልፏል። አንደኛው ውሳኔ ማህበሩ እንደማህበር የሚያገኘውን መጠነኛ ክፍያ እንደመነሻ የ250 ሺ ብር ድጋፍ ለማድረግ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ገንዘቡን ገቢ አድርጓል። ሁለተኛው ውሳኔም የማህበሩ አባል የሆኑና አባል ያልሆኑ የግል ተቋማት በሙሉ አገራዊ ለሆነው ጥሪ ምላሽ መስጠት እንዲችሉ በማሰባሰብ ያላቸውን አገራዊ ስሜት ማንጸባረቅ እንዲችሉና ቃል እንዲገቡ አድርጓል።

በአገሪቱ 310 የሚደርሱ የግል ተቋማት ስለመኖራቸው ዶክተር ሞላ አስታውሰው፤ ነገር ግን ከእነዚህ ተቋማት መካከል ጦርነቱ እየተካሄደ ባለበት ትግራይ እና አማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ ተቋማትን ማሳተፍ የማይቻል ነው ። እነዚህን ሁለት ክልሎች ግምት ውስጥ በማስገባት ቢያንስ 200 ተቋማትን በማሳተፍ አንድ ተቋም በትንሹ 100 ሺ ብር እንዲያዋጣ አለፍ ሲልም ከ100 ሺ በላይ እናዋጣለን የሚል ካለም የቻለውን እንዲያደርግ ዕድሉ ተሰጥቷል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ተቋማቱ አገራዊ ለሆነው ጥሪ ምላሽ መስጠት እንዲችሉ የሚል መነሻ በመያዝ በትንሹ 20 ሚሊዮን ብር ለአገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ለማድረግ ተስማምተው ቃል ገብተዋል።

ተቋማቱ በማህበሩ በኩል ይህን ድጋፍ ያድርጉ እንጂ በየአካባቢያቸው የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉ የሚገኙ ስለመሆኑ ዶክተር ሞላ አስረድተዋል። በተለይም ባለፈው ዓመት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ በቀዳሚነት የተጎዳው የትምህርት ዘርፍ ነው። አሁንም ጦርነቱ እያስከተለ ባለው ሁለንተናዊ ጉዳት በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ የፈጠረው ጫና አለ። ያም ሆኖ ግን ሁሉም ነገር አገር ሲኖር ነውና ተቋማቱ አገርን በማስቀደም ሁለንተናዊ ድጋፍ ማድረግ የግድ መሆኑን አምነው ተሳትፏቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።

 በቀጣይም አገር ለምታደርገው ጥሪ ሁሉ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ እንደሆኑና ለአንዲት ኢትዮጵያ የሚሰስቱት ሀብትና ንብረት እንዲሁም የሕይወት መስዋዕትነት የለም በማለት ያረጋገጡ መሆኑንም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም 200 የሚደርሱ የኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለአገር መከላከያ ሠራዊት 20 ሚሊዮን ብርና ከዛም ባላይ ድጋፍ ለማድረግ በገቡት ቃል መሠረት ፎርም እየሞሉ የሚገኙ ሲሆን ተቋማቱ ገንዘቡን ለዚሁ አገልግሎት በተዘጋጀው አካውንት ገቢ በማድረግ ገቢ ያደረጉበትን ደረሰኝ እንዲሰጡ ተደርጓል። ማህበሩም ድጋፉ ምን ላይ እንደደረሰ ተከታትሎ የሚያሳውቅ ይሆናል።

ተቋማቱ አገራዊ ለሆነው ጥሪ በማህበሩ አማካኝነት እያደረጉ ካለው የገንዘብ ድጋፍ ባለፈ ባሉበት አካባቢ ሁሉ ከራሳቸው ተቋሞች ተማሪዎቻቸውንና ሠራተኞቻቸውን በማሳተፍ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉ ይገኛሉ ። ለአብነትም የደም ልገሳ፣ የስንቅ ማሰባሰብ ሥራ እየሠሩ ሲሆን ከአንድ ኪሎ ማኮረኒ ጀምሮ የምግብ ሸቀጦችን በማሰባሰብ በጦርነቱ ቀጥታ ተሳታፊ ለሆነው የመከላከያ ሠራዊትና ለተፈናቃዮች ተደራሽ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ ይገኛሉ።

ማንኛውም ሰው በተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ጠንክሮ ለመሥራትም ሆነ ስኬታማ ለመሆን የሚሰራበት አካባቢ ሰላም መሆን የግድ ነው። ታድያ ይህን የተረዱት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርት ሚኒስቴር በጠራው አስቸኳይ አገራዊ ጥሪ ላይ በመገኘት እያንዳንዳቸው 100 ሺ ብርና ከዛም በላይ ድጋፍ ለማድረግ ከመወሰናቸው ባሻገር ለአገር የሚከፈል ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል እንዲሁም ግንባር ድረስ በመሄድ አውደ ውጊያውን ለመቀላቀል ያላቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል። ለዚህም ምክንያታችን በተሰማሩበት የትምህርት ዘርፍም ሆነ በሌላ ስኬታማ መሆን የሚቻለው አገር ሰላም ስትሆንና ኢትዮጵያ ስትኖር ብቻ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

አገሪቷ በተለያየ ጊዜ የሚገጥሟትን ችግሮች በጀግኖች ልጆቿ እየተሻገረች ያለ መሆኑ ይታወቃል። በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ያሉ ዜጎች ለአገር እያበረከቱ ባለው አስተዋጽኦ እነርሱም ተጠቅመው ለማህበረሰቡና ለአገር የሚተርፍ ሥራ ሰርተው ስኬታማ ሲሆኑ ይታያል። ከእነዚህም አንዱና ዋነኛው የትምህርት ዘርፍ ነው። ትምህርት ለአንድ አገር ዕድገት ወሳኝና ችግር ፈቺም እንደሆነ ይታመናል። ታድያ መልካምና አገሩን የሚወድ ብቁና ንቁ ዜጋን በመፍጠር በኩል ትልቅ ድርሻ ያላቸው እነዚህ ተቋማት በምን ቁመና ላይ ይገኛሉ ስንል ላነሳነው ጥያቄ ዶክተር ሞላ ሲመልሱ፤

በተለያየ ጊዜ አገሪቷ የሚገጥማትን ችግር በዘላ ቂነት መፍታት የሚቻለው ለትውልዱ ጥራትና አግባብነት ያለው ትምህርት በመስጠት እንደሆነ አንስተው ጥራትና አግባብነት ያለው ሲባልም ሙሉ ለሙሉ ጥራቱን ጠብቆ ነገር ግን ለአገር የማይጠቅምና ችግር ፈቺ መሆን ካልቻለ አግባብነቱ ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል። ስለዚህ ምንም ይሁን ምን አገሩን በታማኝነት የሚያገለግል ስብዕና ያለውና ብቁ ዜጋ መፍጠር የትምህርት ዋና ዓላማው መሆኑ ከጥራት ባሻገር አግባብነት ባለው ትምህርት ትውልዱን መቅረጽ ያስፈልጋል።

የትምህርት ዓላማ ይህ ሆኖ ነገር ግን ከዚህ ውጭ በሆነ አካሄድ ከተመራ ትምህርት አስፈላጊ አይደለም ያሉት ዶክተር ሞላ፤ ከዚህ አንጻር እያንዳንዱ ተቋም ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ትውልዱ ለወገንና ለአገሩ የሚያስብ አገር ወዳድና ብቁ ዜጋ ሆኖ እንዲቀረጽ የድርሻቸውን ይወጣል። እንዲወጣም ነው የሚሠራው። አገሩንና ህዝቡን የሚወድ ዜጋ ማፍራት ከተቻለ አገር በማንኛውም ጊዜ ለሚገጥማት ችግር ትውልዱ የመፍትሔ አካል በመሆን ምላሽ መስጠት ይችላል። ህዝብና አገርን የሚጠቅም አዳዲስ አስተሳሰቦችን በማምጣትም ትርጉም ያለው ሥራ ይሰራል። በዚህም አገር ታድጋለች በማለት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ኅዳር 25/2014

Recommended For You