«ለህግ የበላይነት መከበር ባሳዩት ፅናት የተሰጣቸው ሹመት ተገቢ ነው» የምክር ቤት አባላት

ባለፉት ሰባት ወራት በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ባህል ለማጎልበት የተጀመረው የአስተሳሰብ ለውጥ እውን እንዲሆን አስፈፃሚውን አካል በአዲስ መልክ የማደራጀት ሥራ ሲከናወን ቆይቷል፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎችን እንደ አዲስ ከማደራጀት ጀምሮ የሁሉንም ተቋማት አቅም የማጎልበት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በዚህ መሰረትም ተቋማቱን የሚመሩ አካላትን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት እያቀረቡ ሹመት ተሰጥቷቸዋል፡፡

የተጀመረውን የዴሞክራሲ ምዕራፍ በማስቀጠል ረገድ በትናንትናው እለት በምክርቤቱ አባላት በአብላጫ ድምፅ ተመርጠው የተሾሙት የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ብርቱካን ሚደቅሳ አንዷ ናቸው፡፡ አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው የምክርቤቱ አባላት ተሿሚዋ ህዝቡ የተጠማውን ሰላማዊና ፍትሃዊ ምርጫ የተሳካ ለማድረግ በፅናት ይሰራሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ይገልፃሉ፡፡

«በአገራችን የምርጫን ታሪክ ተከትሎ ይከሰቱ የነበሩት ችግሮችን በመፍታት ረገድ እንደ ወይዘሪት ብርቱካን ያሉ አመራሮችን መሾም በመቻሉ ከፍተኛ ደስታ ነው የተሰማኝ» በማለት አስተያየታቸው የሰጡት በምክር ቤቱ የግብርና ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ነጋልኝ ዮሴፍ ናቸው፡፡ በተለይም ህግን በማስከበር ረገድ ሰፊ ልምድና እውቀት ያላቸው በመሆኑ በከፍተኛ ብቃት ተቋሙን ይመሩታል የሚል እምነት እንዳላቸውም ነው የተናገሩት፡፡

ከወይዘሮ ብርቱካን የምጠብቀው ያላቸውን ልምድና እውቀት ተጠቅመው ህዝቡ እስካሁን ድረስ ለተራበው ፍትህ እርካታ ያመጣሉ ብለው እንደሚጠብቁ የተናገሩት አቶ ዮሴፍ፤ በስራቸው ላይ የሚያጋጥማቸውን እንቅፋቶች ያላቸውን ልምድ በመጠቀም በመፍታት ፍትሃዊ ምርጫ እንዲካሄድ ያደርጋሉ ብለው እንደሚጠብቁም ይገልፃሉ፡፡

አቶ ዮሴፍ በአዲስ መልክ የሚደራጀው ምርጫ ቦርድ በአገሪቱ ውስጥ የሚካሄደው ምርጫ ነጸ፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባዋል፡፡ በዚህ ረገድ የሚታዩ ክፍተቶች ከገዢው ፓርቲም ሆነ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በመመካከር ቀጣዩ ምርጫ በሰላም እንዲከናወን ለማድረግም ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ፡፡

« የምርጫ ጉዳይ በተነሳ ቁጥር የሚታሰበው መጭበርበር ነው፡፡ ይህም ከመጠራጠር የሚመጣ በመሆኑ ተሿሚዋ ማስቀደም ይገባቸዋል ብዬ የማምነው በህዝቡ አዕምሮ ያለው መጥፎ አመለካከት እንዲፋቅ ነፃ የሆነ አመራር መስጠት ይገባቸዋል» በማለትም አቶ ዮሴፍ ተናግረዋል፡፡

ሌላዋ የምክር ቤት አባል ወይዘሮ እቴነሽ ዘለቀ በበኩላቸው፤ «የወይዘሪት ብርቱካን መሾም በአገራችን የሴቶች ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን ያሳያል፤ ለውጡንም ተከትሎ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው ተጠናክሮ እየቀጠለ መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡ ተሿሚዋ ባላቸው የሥራ ልምድ፣ የትምህርት ዝግጅት፣ ለህግ የበላይነት መከበር ያሳዩት ፅናት የተሰጣቸው ሹመት ተገቢ ነው » ብለዋል፡፡

ተሿሚዋ ከዚህ ልምድ በመነሳት የአገሪቱ ምርጫ ተዓማኒና ፍትሃዊ እንዲሆን አጠቃላይ የዴሞክራሲ ስርዓቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የተናገሩት ወይዘሮ እቴነሽ በተለይም የህዝቡን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ ትኩረት መስጠት እንደሚገባቸው አመልክተዋል፡፡

አቶ ዮሃንስ ካሳሁን የተባሉ ሌላ የምክርቤት አባላትም በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ፡፡ በተለይም በአገሪቱ የተጀመረው ሪፎርም ወደፊት ከግብ እንዲደርስ ከማድረግ አኳያ ተሿሚዋ በዕውቀትም በልምድ የተሻሉ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ «እርሳቸው በህግ ካላቸው እውቀትና ልምድ ባሻገር የሰብዓዊ መብት ተሟጋች በመሆናቸው ለህዝብ ድምፅ መከበር በቀናኢነት ይሰራሉ ብለን እናምናለን» ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቀሪዎቹ የቦርድ አባላት ምልመላ ሂደት ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባና ሁሉንም አካላት ማሳተፍ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል፡፡

በዚሁ ምርጫ ወቅት ከምክር ቤቱ አባላት ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ከዚህ ቀደም የተፎካካሪ ፓርቲ አባል የነበሩ በመሆናቸው ነፃና ገለልተኛ ምርጫ እንዳይካሄድ የሚያደርግ ጥርጣሬ እንደሚፈጥርና ሹመታቸው ጥያቄ እንደሚያስከትል ሃሳብ ተሰንዝሮ በተሰጠው ምላሽ፡-

ተሿሚዋ የህግ እውቀታቸው ብቻ ሳይሆን ለመንግሥትም ቢሆን አግባብ ባልሆነ መንገድ እጅ እንደማይሰጡ፣ ለህግ መከበር ፅኑ እምነት ያላቸው መሆኑ፣ ከዚህ ቀደም በነበራቸው ተሞክሮም መረጋገጡን ዶክተር አብይ ገልፀው፤ ለህግ መከበር ዋጋ ለመክፈልም ዝግጁ መሆናቸውን በተግባር ለኢትዮጵያ ህዝብ ያስመሰከሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ «ተሿሚዋ ተቋሙ ገለልተኛ፣ ነፃ፣ ህግ የሚያውቅ፣ ህግ የሚያከብርና በህግ አግባብ የሚሰራ እንዲሆን ማደራጀት ይችላሉ የሚል ሙሉ እምነት አለን፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በህግ ፊት በእኩል ዓይን መታየት አለበት፤ ህግ ሁሉንም የሚያስተዳድርና የሚገዛ መሆን አለበት የሚል ፅኑ አቋም ያላቸውና ይህንንም ለህዝባቸው በተግባር ያረጋገጡ ሴት ናቸው» ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ተሿሚዋ ፍርድ ቤት ባገለገሉበት ወቅት ባለመደለልና ባለመፍራት ፍትህን በማረጋገጥ የሚታወቁ ድንቅ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በውጭ በኖሩበት ወቅት ናሽናል ኢንዶውመንት በተባለ ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ ሆነው ያገለገሉ፣ ብዙ የዴሞክራሲ ጥያቄ ባለባቸው የምርጫ ጉዳዮች ላይ ልምድ ያላቸውና ተቋሙን በብቃት መምራትም ሆነ ቀጣዩን ምርጫ በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲካሄድ ያደርጋሉ ብለው እንዲሚያምኑ ገልፀዋል፡፡

አዲሷ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ሚደቅሳ በበኩላቸው፤ «ይህን ኃላፊነት ስወስድ በኃላፊነትና በገለልተኝነት እንዲቋቋምና እንዲደራጅ የምፈልገውን ነጻ፣ ሚዛናዊና ገለልተኛ የሆነ የምርጫ ስርዓት እንድንገነባ ካለኝ ፅኑ ፍላጎት ነው፡፡ ምክር ቤቱ ይህንን ኃላፊነት ስለሰጠኝ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡ ነገር ግን በጣም ትልቅ ኃላፊነት እንደሆነ ስለማውቅ ይህን ዕድል በማግኘቴ በትህትና እና በአክብሮት ነው የምወስደው» ብለዋል፡፡

እንደወይዘሪት ብርቱካን ማብራሪያ፤ ቦርዱን ከማጠናከር አኳያ ከዚህ በኋላ በአፋጣኝ መደረግ ያለባቸው ብዙ ተግባሮች አሉ፡፡ እስካሁን ያለው ህግ ነጻ፣ ፍትሃዊና ገለልተኛ ባለመሆኑ የህግ ማሻሻያ እየተደረገ ነው፡፡ እርሱን በአፋጣኝ መፈጻም፤ ሌሎችም አባላት ቦርዱን በገለልተኝነት እንዲያገለግሉ፤በዚህ ጉዳይ ላይ ዋና የሚባሉት ፓርቲዎችም ሀሳባቸውን እንዲገልፁበት የሚደረግ ይሆናል፡፡

«እኔ ማስተባበርና መምራት ይጠበቅብኛል፡፡ የእኔ የሙያ ልምዴ ወይም የሰራኋቸው ስራዎች፣ ያደረግኳቸውና የደረሱብኝም ነገሮች ሁሉንም ህዝብ የሚያውቃቸው ናቸው፡፡ሥራዬን የጀመርኩት በዳኝነት ነው፤በፓርቲ ተሳትፎ ውስጥ እንድገባ ያደረገኝ ለህግ ያለኝ ቀናዊነትና በህግ የበላይነት ላይ የተመሰረቱ ተቋማት ሀገሬ ውስጥ ባለማየቴ ነው፡፡ፍርድ ቤት በነበርኩበት ጊዜ ፍርድ ቤቱ በትክክል የሚሰራ፣ ህግን የሚፈጽም ቢሆን ኖሮ ዛሬ ራሴን እዚህ ስለማግኘቴ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡

«የፓርቲ መሪ ከነበርኩኝ አስር ዓመት አልፎታል፡፡ ከዚያ በፊት የአንድነት ለፍትህ መሪ ነበርኩኝ በእስር ምክንያት ሁለት ዓመት አልመራሁም ፡፡ ከዚያ በኋላ በይፋ ለቅቄያለሁ፡፡ በውጭ ሀገራትም በኖርኩበት ጊዜ ወገንተኛ የሚባሉ የፖለቲካ ሀሳቦችን በማራመድ አይደለም ጊዜዬን ያሳለፍኩት፡፡

«በፓርቲ ውስጥ የነበረኝን ልምድ እንደ አንድ ተጨማሪ ተሞክሮ እንጂ እንደ ጉዳት አላየውም፡፡ ያንን ካደረግኩኝ ደግሜ በራሴ ህሊና ላይ ነው ጉዳት የማደርሰው፡፡ ወገንተኛ መሆን ከፈለግኩኝ ፓርቲ ውስጥ ነው መሳተፍ ያለብኝ» በማለት ተናግረዋል፡፡

አዲስ ዘመን ህዳር 14/2011
በማህሌት አብዱል

Recommended For You