ጎንደር ዩኒቨርስቲ ወደ ነበረበት ሰላም መመለሱ ተገለፀ

በጎንደር ዩኒቨርስቲ በዛሬው ዕለት ወደ ነበረበት ሰላም መመለሱ ተገለፀ።

ተማሪዎች ከቁርስ በኋላ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ወደ ክፍል በሚሄዱበት ጊዜ የተወሰኑ ተማሪዎች ማራኪ ግቢ ላይ “ጥያቄዎች ስላሉን ወደ ክፍል እንዳትገቡ” ብለው መከልከላቸውን ዩኒቨርስቲው አስታውቋል።

ከቆይታ በኋላም በማራኪ ግቢና በአፄ ቴዎድሮስ ግቢ ላይ ሰልፍ በመውጣታቸው ሁኔታው ወደ አላስፈላጊ ግጭት እንዳይገባ ለማድረግ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት፣ አመራሮች፣ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባና የፀጥታ ዘርፍ አመራሮች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ወጣቶች በአንድነት ወደ ግቢዎች ዘልቀው በመግባት ተማሪዎችን የማረጋጋት ስራ ሰርተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ፖሊስና በጎንደር ከተማ የሚገኙ የአማራ ክልል ፖሊስ አባላት በተማሪዎች ጥያቄ ወደ ግቢው ገብተው ሁኔታዎችን የማረጋጋት ስራ ሰርተዋል፡፡

በሰልፉ ላይ በነበረው ሁኔታ 12 ተማሪዎች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታል የተሰወዱ ሲሆን 10 ተማሪዎች ህክምና አግኝተው ተመልሰዋል፡፡

ሁለት ተማሪዎች ደግሞ አስጊ ባልሆነ የጤና ሁኔታ ህክምና እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡

በህክምና ላይ የሚገኙ ተማሪዎችም በራሳቸው በተማሪዎች በተውጣጡ ተማሪዎች እንዲጠየቁና ሁኔታውን አይተው ይበልጥ እንዲረጋጉ የማድረግ ስራ ተሰርቷል፡፡

የማወያየት ስራ ከተሰራ በኋላ በአሁኑ ሰዓት ግቢው ሰላማዊ ሆኖ ተማሪዎችም በተረጋጋ ሁኔታ ላይ ናቸው፡፡

የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ፖሊስና በጎንደር ከተማ የሚገኙ የአማራ ክልል ፖሊስ አባላትም በሰላምና መረጋጋት ተግባሩ ላይ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን የጎንደር ዩኒቨርስቲ አስታውቋል።

Recommended For You